በደብረዘይት የመከላከያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (METEC) የተሰሩ የእርሻ መኪኖች ጥራት የሌላቸው መሆኑ ቅሬታ መፍጠሩ ተነገረ፡፡

ሚያዚያ ፲፭(አሥራ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአማራ ክልል የገዢው መንግስት በእርሻ ስራ ያደራጃቸው ወጣቶች እንዲሰሩበት የተሰጣቸው የእርሻ መኪና ጥራት ዝቅተኛ በመሆኑ ስራቸውን አቁመው ማህበራቸወን ለመበተን መገደዳቸውን ተናገሩ፡፡
በክልሉ ልዩ ልዩ ዞኖች የሚገኙት ቅሬታ አቅራቢ ወጣቶች ከዩኒቨርስቲና ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ትምህርታችውን በመጀመሪያ ዲግሪና በዲፐሎማ ያጠናቀቁ ናቸው፡፡ ወጣቶቹ በእርሻ ስራው ለመሰማራት የሚያስችል ፕሮፖዛል አቅርበው ተቀባይነትን በማግኘቱ ገንዘብ በመቆጠብ ብድር ቢፈቀደላቸውም፤ባቀረቡት የሃሳብ እቅድ ዝርዝር (ፕሮፖዛል) ሳይሆን ንብረቱን ከመከላከያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (METEC) እንዲቀርብላቸው መደረጉ ለችግሩ ዋና ምክንያት መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ትራክተሮች ከፍተኛ የጥራት ችግር ያለባቸው መሆኑን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎች ትራክተሮች ሁለት ወር ሳይሰሩ በመሰባበራቸው ስራቸውን ለማቋረጥ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡
ለገዢው መንግስት ግላዊ ሃብት መሰብሰቢያ ሆኖ በሚያገለግለውና በሃገሪቱ ከሚገኙ አበዳሪ የገንዘብ ተቋማት በላይ ወለድ ከሚጠይቀው የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም በ15 በመቶ ወለድ ተበድረው እንዲገዙ የተደረጉት ቅሬታ አቅራቢዎች፣ በመከላከያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (METEC) የቀረቡትን ትራክተሮች እንዲገዙ መገደዳቸው ለችግር እንደዳረጋቸው ተናግረዋል፡፡
የትራክተሮች ጥራት ዝቅተኛ መሆን ለስራቸው እንቅፋት በመሆኑ ማህበራቸውን አፍርሰው ለመበተን መገደዳቸውን የሚናገሩት ወጣቶች፣ በአሁኑ ሰዓት በየተመረቁበት የሙያ መስክ ስራ ቢፈልጉም ስራ በማጣታቸው በቤተሰብ ጥገኝነት ያለ ስራ በመንገላታት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የመከላከያ ብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ፣ ከሀገሪቱ ሀብት እየወሰደ ራሱን ያስፋፋል እንጂ ለመንግስት ግብር ከፍሎ አያውቅም በሚል ይወነጀላል። ድርጅቱ እጅ ባጠረው ጊዜ በመንግስት እንደሚደጎም፣ የሚተዳደረውም በወታደራዊ ህግ በመሆኑ ኦዲት የሚባል ነገር እንደማይነካው እንዲሁም የአንድ ብሄር የበላይነት ጎልቶ የሚታይበት ተቋም ነው በሚል በተደጋጋሚ ይተቻል።