በደብረብርሐን ዩኒቨርስቲ የታሰሩ ተማሪዎች አልተፈቱም

ጥቅምት ፳፫ (ሀያ ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ከሁለት ቀናት በፊት ከውጤት ጋር በተያያዘ በደብረብርሀን ዩኒቨርስቲ ተቀስቅሶ በነበረው የተማሪዎች ተቃውሞ የታሰሩ ከ50 ያላነሱ ተማሪዎች አለመፈታታቸው ታውቋል።

ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ ተማሪዎችና አንድ የአካባቢው ባለስልጣን ለኢሳት እንደገለጡት ተማሪዎቹ ፣ የታሰሩ ጓደኞቻችን እስካልተፈቱ ድረስ ትምህርት አንጀምርም በማለታቸው ዜናውን እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ትምህርት አልተጀመረም።

በትናንትናው እለት የዩኒቨርስቲው ባለስልጣናት የተማሪዎችን ተወካዮች በመሰብሰብ የውጤት አሰጣጡ መመሪያ መሻሻሉን በመግለጽ ተማሪዎች ተቃውሟቸውን እንዲያቆሙ ተማጽነው ነበር። ተማሪዎች ግን ጓደኞቻችን እስካልተፉ ድረስ በአድማው እንገፋለን እያሉ ነው ።

ዛሬ የጸጥታ ሀይሎች  ከዩኒቨርስቲው አካባቢ መራቃቸውን ለማወቅ ተችሎአል። በጉዳት ላይ የሚገኙ 25 ተማሪዎች የደህንነት ሁኔታ ለማወቅ ያደረግነው ጥረት ግን አልተሳካም።

ባለፈው አመት ሚያዚያ 29 እና 30 ላይ በደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ተከስቶ በነበረው የተማሪዎች ተቃውሞ 21 ተማሪዎች ታስረው 16ቱ ወደ ትምህርታቸው እንዳይመለሱ መታገዳቸው ይታወሳል። በያዝነው አመት ተማሪዎች ትምህርት ለመጀመር ወደ ዩኒቨርስቲው ቢያቀኑም ተይዘው ታስረዋል። ተማሪዎቹ 3 ሺ ብር የዋስትና ገንዘብ ካላስያዙ ከእስር እንደማይፈቱ ተነግሮአቸው እንደነበር ይታወሳል።