በደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ውጥረቱ ቀጥሎአል

ጥቅምት (ስድስት)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-ከተማሪዎች አለባበስ ጋር  በተያያዘ ከቀናት በፊት የተጀመረው የተማሪዎች ተቃውሞ እልባት ሳያገኝ አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመለከተ፡

ትናንትና ከትናንት ወዲያ ምሽት ላይ ጥይት ሲተኮስ ማምሸቱን የገለጹት አንዳንድ የተማሪዎች ቤተሰቦች፣ የተኩሱ ምክንያት ጩሀት የሚያሰሙ ተማሪዎችን ዝም ለማሰኘት ያለመ ነው ብለዋል።

ተማሪዎች በየክፍላቸው ሆነው ተቃውሞ እአሰሙ እንደሚገኙ የገለጹት ቤተሰቦች፣ አንዳንዶች ግቢውን ለቀው ወጥተዋል። ዩኒቨርስቲው አዲስ ባወጣው መመሪያ ውጭ የሚገኙ ተማሪዎቹ እስከ ነገ በግቢው ተገኝተው ሪፖርት ካላደረጉ እንደ አመጽ መሪ ተቆጥረው እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ገልጿል።

አንዳንድ ተማሪዎች በውጭ ለመቆየት የገንዘብ እጥረት ስላጋጠማቸው በግቢው ውስጥ ሆነው ተቃውሞ ለማሰማት መምረጣቸውንም እነዚሁ ወላጆች አክለው ገልጸዋል።

የፌደራል ፖሊስ ዩኒቨርስቲውን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረው በመሆኑ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በተረጋጋ መንፈስ ለመጀመር እንደሚቸገሩ የናጋገርናቸው ሰዎች ገልጸዋል።

መንግስት በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የሚካሄዱ ሀይማኖታዊ  ስርአቶችን በተመለከተ አዲስ መመሪያ ማውጣቱ ይታወቃል።

በጉዳዩ ዙሪያ የዩኒቨርስቲውን ባለስልጣናት ለማናገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።