በደብረማርቆስ ከተማ ውጥረቱ ዛሬም ቀጥሎ ዋለ
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 5 ቀን 2010 ዓ/ም ) አቶ በረከት ስምኦን ደብረማርቆስ ከተማ ላይ ታይተዋል በሚል ከሁለት ቀናት በፊት የተጀመረው ተቃውሞ ዛሬም ቀጥሎ መዋሉን ዘጋቢያችን ከስፍራው ገልጿል። ትናንት በዚሁ ሳቢያ በነበረው ተቃውሞ ቤቶችና ተሽከርካሪዎች መውደማቸው ተመልክቷል።
በዛሬው ዕለትም ህዝቡ የህውሃት ተላላኪዎች ወደ ከተማዋ በመግባት ጥፋት ሊፈጽሙ ይችላሉ በሚል በደብረማርቆስ መግቢያና መውጫ ላይ ከፍተኛ ፍተሸ በማካሄድ የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን አግዶ ውሏል።
ወጣቶች ወደ ከተማዋ የሚያስገባውን ዋና መንገድ በትልልቅ ግንድ፣በመኪና ጎማ እና በሲሚንቶ ቱቦዎች በመዝጋት ከተማዋን የተቆጣጠሯት ሲሆን፣ አመጹ ወደ ደብረ ኤሊያስ በመዛመት መንገድ የተዘጋ መሆኑን በቦታው ከሚገኙ መንገደኞች ለመረዳት ተችሏል፡፡
ይሁንና በዛሬ ተቃውሞ በከተማዋ ንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት የለም፡፡በትላንት አመጽ ከእደሙትና ጉዳት ከደረሰባቸው ሆቴሎች በተጨማሪ የከተማው ከንቲባ መኖሪያ ቤት መቃጠሉን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡የከንቲባው ቤት የተቃጠለበት ምክንያት በቅርቡ በተደረገው ህዝባዊ ውይይት የከማው ወጣቶች ችግራቸውን አንስተው ሲጠይቁ “አብይ ይፍታላችሁ፣ ” የሚል ምላሽ መስጠቱ፣ ህዝብ በማስቆጣቱ እንደሆነ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች ግጭቱ ሰሞኑን በባጃጅ አሽከርካሪዎችና በከተማው አስተዳዳሪዎች እንደተጀመረ ይናገራሉ።
አመጹን ያስነሳው፣ በደብረ ማርቆሱ የድጋፍ ሰልፍና ከዚያ በኋላ በከተማው አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ባንዲራ እና የጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድን ፎቶ ግራፍ በለጠፉ ባጃጆች ላይ የአምስት መቶ ብር ቅጣት መጣሉ ነው።
የከተማው አስተዳደር ተወካዮች በታሪፍ ጭማሪ እንደተቀጡ በመጥቀስ የአመጹን ምክንያት ለማስተባበል ቢሞክሩም፣ ነዋሪዎቹም ሆነ የባጃጅ ሾፌሮቹ ምክንያቱ በታሪፍ ጭማሪ አለመቀጣታቸውን በማብራራት ማስተባበያውን አጣጥለውታል።
ዛሬ ከሰዓት በሁዋላ ተዘግቶ የነበረው ደብረ ማርቆስ መንገድ የሃይማኖት አባቶች ከከተማዋ ወጣቶች ጋር ባደረጉት ውይይትና ምልጃ እና ስምምነት መሰረት መከፈቱን ወኪላችን ዘግቧል።