በደባርቅ ለሶስት ቀን የሚቆይ ከቤት ያለመውጣት አድማ መጀመሩን ተከትሎ ግጭት ተቀሰቀሰ

ኢሳት (ነሃሴ 17 ፥ 2008)

የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎች ለሶስት ቀን የሚቆይ ከቤት ያለመውጣት አድማ ማክሰኞች መጀመራቸውን ተከትሎ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ነዋሪዎች የወሰዱትን ዕርምጃ ለማስቆም ያደረጉት ጥረት ግጭትን ቀሰቀሰ።

የስራ ማቆም አድማ ያካተተውን ተቃውሞ የተቀላቀሉ የደባርቅ ከተማ ሆስፒታል የህክምና ስራተኞች በቅጥር ግቢው ውስጥ በጸጥታ ሃይሎች ድብደባ እንደተፈጸመባቸው እማኞች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።

በጎንደር ባህር ዳር ከተማ የተፈጸመ ግድያን ለማውገዝና በየከተሞቹ እየተካሄዱ ያሉ ተቃውሞዎችን በመደገፍ የከተማዋ ነዋሪ ማክሰኞ  ለሶስት ቀን የሚቆይ ከቤት ያለመውጣትና የስራ ማቆም አድማ መጀመራቸው ታውቋል።

ይሁንና በከተማዋ የሚገኙ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ነዋሪው አድማውን እንዲያቆምና ድርጅቶችን እንዲከፍት ሃይል ቢጠቀሙም ድርጊቱ ወደ ግጭት መለወጡን ነዋሪዎች ለኢሳት አስታውቀዋል።

የጸጥታ ሃይሎች ከነዋሪዎቹ ጋር ያደረጉት ግጭት ለበርካታ ሰዓታት በተኩስ ልውውጥ ውስጥ ቆይቶ የነበረ ሲሆን፣ በትንሹ አስር ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ እማኞች ለኢሳት አስረድተዋል።

በተኩስ ድርጊቱ ጽኑ ጉዳት የደረሰባቸው ነዋሪዎች ወደ ጎንደር ከተማ መወሰዳቸውን የተናገሩት እማኞች ከጸጥታ ሃይሎች መካከልም የተጎዱ መኖራቸውን አከለው ገልጸዋል።

በከተማዋ ለሰባት ሰዓታት ያህል የቆየ የተኩስ ልውውጥ እንደነበር የተናገሩት የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎች የሆስፒታል ሰራተኞችና ሃኪሞች በስራ ማቆም አድማ ለመሳተፍ የወሰዱት እርምጃ በስራ ገበታቸው ላይ ድብደባ እንዲፈጸምባቸው ማድረጉን አክለው አስታውቀዋል።

በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የተወሰደው የሃይል እርምጃ በነዋሪው ዘንድ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን፣ የከተማዋ ነዋሪዎች ለቀጣዩ ሶስት ቀናቶች ከቤት ያለመውጣት አድማ ውስጥ ለመሰንበት መወሰናቸውን ለመረዳት ተችሏል።

በከተማዋ ውጥረት መንገሱን ለኢሳት በሰጡት ቃለምልልስ የገነጹት የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎች ህዝቡ በተለያዩ የሃገሪቱ ቦታዎች ለሚካሄድ ተቃውሞዎች አጋርነቱን ለመግለጽ ውሳኔ መድረሱን አክለው አስረድተዋል።