በደቡብ ጎንደር የተጀመረው ትጥቅ የማስፈታት ዘመቻ ከሸፈ

(ኢሳት ዜና – ሰኔ 30 2009)

በደቡብ ጎንደር እብናት ወረዳ የህውሃት አጋዚ ጦር የገበሬውን ትጥቅ ለማስፈታት ያደረገው ሙከራ መክሸፉ ተነገረ ።

በሰሜን ጎንደር የተጀመረው ገበሬውን ትጥቅ የመፍታት ዘመቻ ወደ ደቡብ ጎንደር ተሻግሯል ።የኢሳት መንጮች እንደገለጹት በደቡብ ጎንደር እብናት ወረዳ ባሉ ቀበሌዎች ትጥቅ ለማስፈታት የአጋዚ ጦር በከፈተው ተኩስ 3 ሰዎች ቆስለዋል ። በእብናት ወረዳ ሰፍሮ የነበረው የህውሃት አጋዚ ጦር በሚንጦች ፣ መልዛ ፣ ጨጨወ አቦ ፣ እና ወፍጮማ በተባሉ አካባቢዎች ዘምቶ በታጠቁ ገበሬዎች ጥቃት ደርሶበታል ተብሏል ። በዚሁ ጥቃት የተበሳጨው የህውሃት ጦር አዛውንቶችን ህጻናትንና ሴቶችን እየደበደበ ወደ እስር ቤት እያስገባቸው መሆኑን ምንጮቻችን ገልጸዋል ።

በሰሜን ጎንደር የተጀመረውን የትጥቅ ትግል ማስቆም ያልቻለው የህውሃት ጦር ሶስት ስልቶችን በመከተል በህዝቡ ላይ ጫና እያደረገ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል ። የህውሃት አጋዚ ጦር በስሜን ደቡብ ጎንደር ህዝቡን ትጥቅ ለማስፈታት የሚጠቀምባቸው ሶስቱ

ስልቶችና ዘዴዎች የሃይማኖት መሪዎች እንዲገዝቱ መላክ ፣ በገንዘብና በማባበያ መደለልና የሃይል እርምጃ መውሰድ የሚሉ ናቸው ። በአማራ ክልል ህዝቡን ትጥቅ ለማስፈታት የተጀመረው ዘመቻ ሊሳካ ያልቻለው የእካባቢው ህብረተሰብ ከሁሉም በፊት ጦር መሳሪያ የነጻነቱ ዋስትና አድርጎ ስለሚወስድ ነው ተብሏል ።

በሰሜንና ደቡብ ጎንደር ያሉ የነጻነት ታጋዮች በጎበዝ አለቃ እየተመሩ አካባቢውን እስካሁን ተቆጣጥረውት ይገኛሉ ። የግንቦት ሰባት አርበኞች የተለያዩ ጥቃቶችን በመፈጸም አገዛዙን እያዳከሙ እንደሚገኙም በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል ።