የካቲት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሰሞኑን በደቡብ ጎንደር ደብረታቦር አካባቢ የተነሳው ከባድ ጉንፋን ሰዎችን ለህልፈት እየዳረገ ቢሆንም የአካባቢው ባለስልጣናትም ሆኑ የክልሉ አመራሮች የወሰዱት ጠንከር ያለ እርምጃ ባለመኖሩ የአካበቢው ህብረተሰብ በጭንቀት ላይ መሆኑን ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ለየት ብሎ በተከሰተው ጉንፋን እስካሁን ስድስት ሰዎች መሞታቸው የታወቀ ሲሆን በተለይ በደብረታቦር ማረሚያ ቤት በሽታው እየተስፋፋ በመሆኑ በበሽታው የተለከፉ ሰዎችን ለማግለል እየተሞከረ ነው፡፡
በሽታው በደብረታቦር ዙሪያ ባሉ ገጠሮች እየታየ ሲሆን ከበሽታው ጋር በተያያዘ ይሁን ወይም በሌላ ባልታወቀ ሁኔታ በሽታው በተከሰተባቸው አካባቢ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተዘጉ መሆኑን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።