ኀዳር ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በፎገራ ወረዳ፣ ወረታ ከተማ በቁሃር ሚካኤል ቀበሌ ነዋሪ የሆነው መንግስቴ ቢምር የተባለ የአካባቢ ሹም የህብረተሰቡን መሳሪያ በማስፈታት ከኢህአዴግ ጋር ሲሰራ ነበር በሚል መገደሉን ተከትሎ፣ እስካሁን በቁጥጥር ስር ያልዋሉት ገዳዮች በተገኙበት እንዲገደሉ መወሰኑን ምንጮች ገልጸዋል።
ከሹሙ ግድያ ጋር በተያያዘ እየተፈለጉ ያሉትና ባለቡት ይገደሉ የተባሉት አርሶ አደር መንጋው አላምር ፣ አርሶአደር በላቸው ውዱ ፣ ሙሉነህ ሙጨ ፣ተማሪ የነበረና በባጃጅ ሾፌርነት የሚተዳደር እንዲሁም አርሶ አደር ገዳሙ በላይ ናቸው።
ፖሊሶችና ካድሬዎች የመንጋውን ቤት ያፈረሱት ሲሆን ፣ ቤቱ ውስጥ የተገኘውን ንብረት ሁሉ ዘርፈዋል።
አርሶ አደሮቹ መጀመሪያ የደህንነት አባሉን ገድለዋል ተብለው ተፈርጀው ነበር በተገኙበት እንዲገደሉ የታዘዘው። ይሁን እንጅ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ እንዴት ይገደላሉ ይባላል የመል ጥያቄ ሲነሳ፣ አርሶ አደሮቹ የ አርበኞች ግንቦት ሰባት አባላት ስለሆኑ ነው ሹመን የገደሉት የሚል አዲስ ክስ ቀርቦባቸዋል። ሟቹ ሹም ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን መሳሪያ ተሸልሟል ፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ ህዳር 4/2008 ዓ.ም በምዕራብ ጎጃም ዞን መራዊ ከተማ የታሰሩት 8 ወጣቶች ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡ ህዳር 4/2008 ዓ.ም በሌሊት ቤታቸውን ተበርብሮ ከታሰሩት መካከል በተለይም የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች የሆኑት አቶ መኳንንት ፀጋዬ እና አቶ እያዩ መጣ ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰባቸው ታውቋል፡፡ ህዳር 4/2008 ዓ.ም ጣቢያ ዘጠኝ ተብሎ ወደሚታወቀው እስር ቤት ተወስደው እንደተደበደቡ የገለፁት ምንጮቹ፣ ህዳር 9/2008 ዓ.ም ፍርድ ቤት ቀርበው ወደ ማረሚያ ቤት እንዲዛወሩ ትዕዛዝ ቢሰጥም ፖሊስ ባህርዳር ከተማ በሚገኘው ጣቢያ ዘጠኝ የተባለ እስር ቤት በመውሰድ እስከ ህዳር 14/2008 ዓ.ም ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ጋዜጣው ዘግቧል።
ፖሊስ እስረኞቹን ወደ ማረሚያ ቤት እንዲያዛውር ትዕዛዝ ተሰጥቶት የነበር ቢሆንም ፣ እስረኞቹ ፍርድ ቤት ቀርበው ጣቢያ ዘጠኝ በተባለው እስር ቤት ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰባቸው በመግለፃቸው ‹‹ለፍርድ ቤቱ ለምን ተደበደብን ብላችሁ ተናገራችሁ?›› በሚል ለተጨማሪ 5 ቀናት ድብደባው እንደተፈፀመባቸው ተዘግቧል። እስረኞቹ ድብደባው የሚፈፀምባቸው ‹‹ለምን የተቃውሞ እንቅስቃሴያችሁን አታቆሙም? ከተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ጋር ያላችሁን ግንኙነት ለምን አታቆሙም?›› እየተባሉ ነው።
ህዳር 4/2008 ዓ.ም ከታሰሩት መካከል መኳንንት ፀጋዬ፣ እያዩ መጣ፣ መምህር ሀብታሙ ጥላሁን፣ ስማቸው ማዘንጊያ ፣ ቄስ ዘላለም ሞትባይኖር፣ አረጋዊ መጣ፣ ሽባባው የኔዓለም እና አብርሃም ተስፋ ሲሆኑ አብርሃም ተስፋ የኢህአዴግ አባል እንደሆነ ጋዜጣው ዘግቧል። ሽባባው የኔአለም ደግሞ የጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለም ወንድም ነው።
እስረኞቹ ለታህሳስ 24 በድጋሜ ለፍርድ ተቀጥረዋል። በሁሉም እሰረኞች ላይ ይህ ነው የሚባል መረጃ ሊቀርብባቸው አልቻለም። በመራዊና በአካባቢዋ በሚገኙ ቀበሌዎች ከ60 ያላነሱ ወጣቶች አዲስ አበባ እና ባህርዳር ታስረው ይገኛሉ። አብዛኞቹ ከአርበኞች ግንቦት7 ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል ነው የታሰሩት።
የህክምና ባለሙያ የሆነው መኳንንት ጸጋዬ ከልጆቹና ባለቤቱ ፊት ከፍተኛ ድበደባ ተፈጽሞበታል። ከዚህ ቀድምም በተደጋጋሚ ስራ እንዳይሰራ የአካባቢው ሹሞች ከፍተኛ ተጽኖ ሲያደርጉበት ነበር።