ጥር ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በላይጋይንት ወረዳ ከታች ነጋላ ነዋሪዎች መካከል በቀበሌ 23፣24 እና 26 በከፍተኛ ሁኔታ በድርቅ ከመጎዳታቸው ጋር ተያይዞ በተነሳ በሽታ ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ አባዎራዎች ለሞት መዳረጋቸውን በርካቶችም የበሽታ ሰለባ ሆነው እንደሚገኙ የአካባቢው ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከ1100 በላይ የቤት እንስሳት ማለቃቸውንም አክለው ተናግረዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ሰሞኑን እርዳታ ለመጠየቅ ወደ ዛጎቻ ከተማ አምርተው ጥያቄ ሲያቀርቡ የሚያሳይ ምስል ኢሳት ደርሶታል። ነዋሪዎቹ አፋጣኝ እርዳታ ካልደረሰላቸው በስተቀር እስካሁን ከደረሰው የከፋ ጉዳት ሊደርስባቸው እንደሚችል ተናግረዋል።
ኢሳት ስለሞቱት ሰዎች የአካባቢውን ባለስልጣናት ለማናገር ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።
የኢትዮጵያ ረሃብ የአለማቀፍ የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት እየሳበ ሲሆን፣ የተለያዩ የውጭ ድርጅቶች አፋጣኝ እርዳታ እንዲቀርብ መወትወት ጀምረዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አንድ አምስተኛ የሚሆነው ወይም ከ20 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን በያዝነው አመት በረሃብ ሊጠቁ ይችላሉ ሲል ገልጿል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ ባንኪ ሙን በድርቅ የተጎዱ አንዳንድ አካባቢዎችን የፊታችን እሁድ ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በሌላ ዜና ደግሞ ቤዛ እንሁን የበጎ ፍቃደኞች ስብስብ በድርቅ ለተጎዱ ኢትዮጵያዊያን እርዳታ ለግሷል።
በበጎ ፈቃደኛ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች አነሳሽነት የተቋመው ቤዛ እንሁን የበጎ ፈቃደኞች ስብስብ ለወገን ደራሽ ወገን ነው በማለት ያሰባሰቡትን 15 ሽህ ብር ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ጋር በጋራ በመተባበር በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን ሲሬ ወረዳ በአካል በመገኘት ለተጎጂዎች አድርሰዋል።
የማኅበሩ አባላት ይህ የመጀመሪያ ዙር የረድኤት ልገሳቸው ሲሆን ቀጣይም ለችግረኛ ኢትዮጵያዊያንን ማገዙን እንደሚቀጥሉበት ወጣቶቹ አስታውቀዋል። የእርዳታ አሰጣጡን በተመለከተ በነገው ዕለት በ‹‹ቤዛ እንሁን›› ህዝብ ግንኙነት በኩል መረጃዎችን በዝርዝር እንደሚያቀርቡ ኤሊያስ ገብሩ በፌስቡክ ገጹ ዘግቧል።
በኢትዮጵያ ያለው የእርሃብ ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ ዜጎች በማኅበሩ ጥላ ስር በመሰባሰብ በተግባር ለወገን ደራሽ አለኝታ መሆናቸውን ያሳዩ ዘንድ ወጣቶቹ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።