(ኢሳት ዲሲ–ጥር 27/2011)በደቡብ ጎንደር በመስጊድ ላይ የደረሰው ቃጠሎ ኢትዮጵያ ሰላም እንዳትሆን በሚፈልጉ አካላት የተፈጸመ መሆኑን የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት አስታወቀ፡፡
በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን እሰቴ ከተማ ቀበሌ 03 ላይ ሁለት መስጊዶች መቃጠላቸው ታውቋል።
የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ጸሃፊ ሼህ መሐመድ ሐሰን ድርጊቱ ለበርካታ ዘመናት በፍቅር የኖሩትን ህዝቦች ለማለያየት ያለመና ሁለቱንም ወገኖች የማይወክል ነው ብለዋል፡፡
የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች ባዘጋጁት የሰርግ ሥነ ሥርዓት ላይ በወረቀት እና ማስጌጫ ዳሱን የማስዋብ ሥራ እየተከናወነ እያለ ነው የድርጊቱ መነሻ የተከሰተው ፡፡
ከማስዋቢያው ጋር ከማተሚያ ቤት አብሮ የመጣ የማርያም ስዕል ከሌሎች ማስዋቢያ ቁርጥራጮች ጋር ወድቆ መገኘቱም የጸቡ መነሻ ሆኗል ነው ያሉት፡፡
ጉዳዩ እንደተፈጸመ ስዕሉን ማን እንዳመጣው ስላልታወቀ የሁለቱም ኃይማኖቶች አማኞች በተገኙበት ስዕሉ ተነስቶ ሁኔታው ተረጋግቶ ነበር፡፡
‹‹በኋላ ላይ ግን ይህን ምክንያት በማድረግ ሁለት መስጊዶች ተቃጥለዋል፤ ሌላ ሶስተኛ መስጊድ ላይም ድብደባ ተፈጽሟል፤ሱቆችም ተዘርፈዋል›› ነው ያሉት ሼህ ሙሃመድ፡፡
ድርጊቱ የክርስትናም ሆኑ የእስልምና አማኞችን የማይወክል ነው ሲሉም ሼህ ሙሃመድ አውግዘውታል፡፡
ኢትዮጵያ ሰላም እንዳትሆን የሚፈልጉ የፖለቲካ አራማጆች የዘሩት ጥል አልሆን ሲላቸው ወደ ሃይማኖት እየተዘዋወሩ መሆናቸውን በመግለጽ።
ኢትዮጵያውያን የሃይማኖት ልዩነት ሳይለያየን ለብዙ ዓመታት በሰላም እና በፍቅር ኖረናል፤አሁንም እንኖራለን፤የሴረኞችን ድርጊት አውግዘን በፍቅራችን እቀጥላለን ሲሉም የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ጸሃፊ ሼህ መሃመድ ሀሰን አረጋግጠዋል።
‹‹ሃይማኖት ሀገር መገንቢያ እንጂ ሀገር ማፍረሻ አይደለም›› ያሉት ዋና ጸሃፊው በሃይማኖቶች ገብተው ኢትዮጵያን ለመበታታን የሚጣጣሩ የፖለቲካ ቅጥረኞችን ሁሉም ዜጋ ሊያወግዛቸው እንደሚገባ ነው የጠየቁት፡፡
ድርጊቱ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮችን እንደማይወክልም ገልጸዋል፡፡
ህዝቡን የሚያረጋጋ እና ድርጊቱን እነማን እንደፈጸሙት የሚለይ ቡድንም ወደ ስፍራው መሄዱን ነግረውናል፡፡
ህዝበ ሙስሊሙ ድርጊቱ የፖለቲከኞች እንጂ የአማኞች አለመሆኑን ተረድቶ በተለመደው ፍቅሩ እንዲቀጥልም ሼህ መሀመድ ሀሰን ጥሪ አቅርበዋል።