በደቡብ ክልል ከፖሊስ መጋዘን የጦር መሳሪያ ተዘረፈ

ነሀሴ ፲ (አስር) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በደቡብ ክልል ከሚገኘው ደራሼ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት መጋዘን ውስጥ  የጦር መሳሪያ መዘረፉ ተገለፀ፡፡

የጦር መሳሪያው በጊዜያዊነት በመጋዘን ተሰብስቦ የነበረው በአሁን ወቅት በ“አሌ” ወረዳ የሚገኘው ህዝብ፤ በደራሼ ልዩ ወረዳ ስር በነበረበት ወቅት ነው።

በ1997 ዓ.ም የወረዳ ህዝብ ላቀረበው ራስን ችሎ የመዋቀር ጥያቄ አመራሩ ተግባራዊ ምላሽ እንደሚሰጥ  ቃል ቢገባም፤ በወቅቱ በነበረው አገር አቀፍ ምርጫ  በአካባቢው ቅንጅት ማሸነፉን ተከትሎ ቃል የተገባው ሳይተገበር በመቅረቱ፤በህዝቡ ዘንድ ቅሬታ ተፈጥሮ መቆየቱን የፍኖተ-ነፃነት ዘገባ ያስረዳል።

 

በዚህም ምክንያት በ2002 ዓ.ም መሳሪያ ያላቸው የአካባቢው ማህበረሰብ አባላት ከፖሊስ እና አጋአዚ ጦር ጋር ውጊያ ገጥመው ከፍተኛ የሰው ህይወት እና ንብረት ጠፍቶ እንደነበር ያወሱት የጋዜጣው ምንጮች፤ በስተመጨረሻም በአካባቢው ሽማግሌዎች ጥረት ግጭቱ መብረዱን  ጠቁመዋል፡፡

እንደ ነዋሪዎቹ ገለፃ፤ከግጭቱ መርገብ በኋላም ነው የልዩ ፖሊስ ኃይል ከማኀበረሰቡ የወረሳቸውን መሳሪያዎች በወረዳው ፖሊስ ጽ/ቤት ጊዜያዊ መጋዘን ያስቀመጠው።

ሆኖም፤ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የወረዳው ፖሊስ አባላት ለጋዜጣው እንደነገሩት ከሳምንት በፊት፤ማለትም ሐምሌ 27 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች መጋዘኑን ሰብረው በመግባት በውስ   የተቀመጡትን ክላሽንኮቭ ጠመንጃዎችን እና ሌሎች የጦር መሳሪያዎችን ዘርፈው ተሰውረዋል።

ስለጉዳዩ የተጠየቁት የወረዳው ምክትል አስተዳደር አቶ ግንኙነት ኪንተቦ ፦ “የተባለው ነገር ስህተት ነው” በማለት መልስ ከሰጡ በኋላ፤ የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ስለ ተዘረፈው መሳሪያ ዜና እንዳይሰራ ጋዜጠኞቹን  ለማስፈራራት መሞከራቸውን ፍኖት አጋልጧል።

አንዳንድ የወረዳው ፖሊስ ጽ/ቤት አባላት በበኩላቸው በ2002 ዓ.ም ግጭት ወቅት ከማኅበረሰቡ ስለተሰበሰቡት የጦር መሳሪያዎች ዝርዝር ሪፖርት ለመንግስት አካል  መቅረቡን እንደሚጠራጠሩ ተናግረዋል።

በመሆኑም  የተዘረፉትም መሳሪያዎች ወደ ህገወጦች እጅ ገብተው የአካባቢውን ፀጥታ ከመናጋቱ በፊት የሚመለከተው አካል ጉዳዩን አጣርቶ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ አሣስበዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት በዚሁ ወረዳ ዝርፊያ የፈፀሙ ሁለት ፖሊሶች በወረዳው አስተዳደር በነፃ እንዲለቀቁ መደረጋቸው ይታወሳል፡፡

____________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide