በደቡብ ክልል በጉራፈርዳ ወረዳ  በመዠንገርና ደገኛ በሚባሉት ነዋሪዎች መካከል በተነሳው ግጭት ብዙ ነዋሪዎች መገደላቸው ተሰማ

መስከረም ፴(ሠላሳ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በቅርቡ በቴፒ አካባቢ በመዠንገር ብሄረሰብና ደገኛ በሚባሉት ነዋሪዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት ተባብሶ በርካታ ህዝብ ካለቀ በሁዋላ የመከላከያ ሰራዊት ወደ አካባቢው ገብቶ ለጊዜያው ያበረደው ቢመስልም፣ ግጭቱ ወደ ጉራፈርዳ ወረዳ አቅጣጫ ተዛምቶ እስካሁን

ከ20 ያላነሱ ሰዎች መገደላቸውና በርካቶችም በመሰደድ ላይ መሆናቸውን የአካባቢው የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። ምንጮች እንደሚሉት ካለፉት ሶስት ቀናት ጀምሮ የተነሳው ግጭት በማየሉ፣ በተለይ ሴቶችና ህጻናት አካባቢውን እየለቀቁ በመሰደድ ላይ ሲሆኑ፣ ዛሬ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን የጫኑ መኪኖች ወደ አካባቢው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ግጭቱ ወደ ሌሎች ከተሞች ይዛመታል በሚል በፍርሃት መዋጣቸውን ተናግረዋል

መስከረም መግቢያ ላይ በተነሳው ግጭት ከተፈናቀሉ ነዋሪዎች መካከል የተወሰኑት ወደቦታቸው ቢመለሱም፣ አሁንም በስጋት እንደሚኖሩ ይናገራሉ። ኢሳት ከኢዲቶሪያል ፖሊሲው ምክንያት ለህዝብ ይፋ ያላደረጋቸው በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ህጻናት፣ እናቶችና ጎልማሶች ፎቶግራፎች ደርሰውታል።

መንግስት እየተከተለ ያለው ዘርን ማእከል ያደረገ ፖሊሲ ለግጭቱ ዋናው መንስኤ ቢሆንም፣ በአካባቢው የሚታየው የመሬት ቅርምት ለግጭቱ መባባስ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች ይገልጻሉ።

ስቱዲዮ ከገባን በሁዋላ የደረሰን ዜና እንደሚያመለክተው በጉራፈርዳ አካባቢ የተነሳው ግጭት አስከፊ በሆነ ሁኔታ ቀጥሎአል።