ኢሳት ዜና:- ማክሰኞ እለት ከወረዳና ከልማት ጋር በተያያዘ የተነሳው ተቃውሞ ሌሊቱን በሙሉ አድሮ በማግስቱም ተጠናክሮ መቀጠሉን ከስፍራው
የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የአካባቢው እና የክልሉ ፖሊስ ሁኔታውን መቆጣጠር ባለመቻላቸው በ7 መኪና የተጫኑ የፌደራል ፖሊስ አባላት በስፍራው ተገኝተዋል። የክልሉና የፌደራል ባለስልጣናትም በአካባቢው ተገኝተዋል።
እስካሁን ድረስ ከ26 አላነሱ ሰዎች ተይዘው መታሰራቸውንና 4 ግለሰቦችም ተደብድበው መታሰራቸውን ለማወቅ ተችሎአል።
ከተሳሩት መካከል አቶ አድነው ማሞ፣ ተፈራ ታደሰ ፣ ምትኩ በቀለ፣ ከበደ ኮኑ፣ ግርማ ጌታቸው ፣ ካሰች ተገኝ፣ አብነት አግደው፣ዘነበ ገርገራ፣ ጥረቱ ሀይሌ ይገኙበታል።
ከተለያዩ ቀበሌዎች እየተመመ ወደ ከተማው የጎረፈው ህዝብ የታሰሩት ተወካዮቻችን ካልተፈቱ በስተቀር ተቃውሞአችንን እንቀጥላለን ማለታቸውን ያነጋገርናቸው አካባቢው ተወላጆች ገልጸዋል።
ትምህርት ቤቶችና ሌሎች ማህበራዊ አግልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በሙሉ የተዘጉ ሲሆን፣ የአካባቢው ነዋሪዎችም ” ዳውሮ ላይ የመንግስት ስርአት የለም፣ ልማት የለም፣ እስራትና ድብደባ ይቁም፣ የሚሉ መፈክሮችንና “ነጻነት አጣን እኛ የዋካ ልጆች፣ ስርአቱ ገደለን የዋካን ልጆች” የሚል ይዘት ያለው መዝሙር ሲዘምሩ ተሰምተዋል ።