ታህሳስ 16 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በክልሉ በተጀመረ ግምገማ ፣ ከ5 0 ያላነሱ ሰዎች በሙስና ሰበብ ተባረዋል።
የግምገማው ዋነኛ ነጥብ በዳውሮ ዞን በዋካ ከተማ ከተነሳው ብጥብጥ ጋር በተያያዘ ሲሆን፣ የፌደራሉ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ መረጃው በአለም እንዲሰራጭ በማድረግ በኩል እጃቸው አለበት ብሎ የጠረጠራቸውን ባለስልጣናት በማባረር በአዲስ ሰዎች እየተካ ነው።
የመባረር እጣው ከደረሳቸው ባለስልጣናት መካከል የደቡብ ክልል የፖለቲካ ጉዳዮች ሀላፊ የነበሩት አቶ አለማየሁ አሰፋ አንዱ ሆነዋል።
አቶ አለማየሁ አሰፋ ” የኔነህ የአእምሮ በሽተኛ ነበር የሚል የፈጠራ ወሬ ” እንዲሰራጭ በማድረጋቸው በዋካ ህዝብ ዘንድ በከፍተኛ ደረጃ የሚጠሉ ሰው መሆናቸውን የአካባቢው ተወላጆች ለኢሳት ተናግረዋል።
ኢህአዴግ እኝህን ሰው ያባረራቸው በደቡብ ክልል እየጨመረ የመጣውን የህዝብ ብሶት ለማስታገስ አልቻሉም በሚል ምክንያት ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዛሬው እለት አንድ አርሶ አደር በካቢኔ አባላት ፊት ራሱን ለመስቀል ሙከራ አድርጎ በተዓምር መትረፉን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የዳውሮ ዜን የተለያዩ ወረዳዎች ካቢኔ አባላት በዋካ ከተማ የተፈጠረውን ችግር እየገመገሙ ባሉበት ወቅት ከጌኛ ወረዳ የመጡ አርሶ አደር ራሳቸውን በገመድ ሰቅለው ለመግደል ሲሞክሩ በፖሊስና በካቢኔው አባላት ተርፈዋል።
አርሶአደሩ ይህን እርምጃ የወሰዱት የወረዳው ካቢኔ አባል ወንድም መሬቴን ቀምቶ በጉልበት ወስዶብኛል በሚል ነው።
አርሶ አደሩ በተደጋጋሚ ለሚመለከታቸው አካላት ቢያመለክቱም መፍትሄ የሚሰጣቸው ሰው ግን አላገኙም።
በዚህም የተነሳ ራሳቸውን ለማጥፋት መወሰናቸውን የተርጫ ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጠዋል።
ግለሰቡ በአሁኑ ጊዜ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደሚገኙም ለማወቅ ተችሎአል።
መምህር የኔሰው ገብሬ ራሱን በእሳት አቃጥሎ ከገደለበት ጊዜ ጀምሮ አንድ የመንግስት ሰራተኛ ራሱን አንቆ ለመግደል መሞከሩን፣ መሬቱዋን የተቀማች ሌላ ሴት አርሶ አደር ደግሞ ገደል ውስጥ ገብታ ራሱዋን ማጥፋቱዋን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጠዋል።
እንዲህ አይነቱ እርምጃ በተደጋጋሚ መከሰቱን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ የአካባቢው ህዝብ በኢህአዴግ አጋዛዝ ስር ላለመኖር መቁረጡን የሚያሳይ ነው ሲሉ አክለዋል።