ኀዳር ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢሳት ያነጋገራቸው ወጣቶች እንደገለጹት፣ በወላይታ ሶዶ ከ1 ሺ የማያንሱ በራሪ ወረቀቶች ተበትነዋል። ራሳቸውን ያደራጁት ወጣቶች በፖሊስ፣ በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የገበያ ማእከላት የአርበኞች ግንቦት7 ሊ/መንበር የፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ን ፎቶ እንዲሁም የቅስቀሳ መልእክቶችን የያዙ ወረቀቶችን በግድግዳዎች ላይ ለጥፈዋል። ፖሊሶች ወረቀቶችን በመቅደድ ተጠምደው ማርፈዳቸውን፣ በከተማው ውስጥ ትልቅ የመነጋገሪያ ርእስ መፍጠሩንም ወጣቶች ለኢሳት ገልጸዋል።
በአርባምንጭ፣ ቁጫና ጎፋ (ሳላ) በርካታ ወረቀቶች ተበትነዋል። በእነዚህ አካባቢዎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን የሚያስተባብረው ወጣት እንደገለጸው፣ ወረቀት መበተኑ በህዝቡ ውስጥ ትልቅ መነቃቃት ፈጥሯል ብለአል። ህዝቡ ወረቀቶችን በደንብ መመልከቱንና ለካ መንግስትን የሚገዳደር ሃይል እየተፈጠረ ነው የሚል አስተያየቶች እንደደረሱዋቸው አስተባበሪዎች ገልጸዋል።