ኢሳት (ህዳር 1 ፥ 2009)
በደቡብ ክልል የደቡብ ኦሞ ዞን ስር በሚገኙ ሁለት ቀበሌዎች በጸጥታ ሃይሎችና በሃመር ተወላጆች መካከል በተፈጠረ ግጭት አንድ የፖሊስ አባል መገደሉንና በአካባቢው ውጥረጥ መንገሱን እማኞች ለኢሳት አስታወቁ።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ በአልድባ ቀበሌ እና በአካባቢው በሚገኙ አጎራባች ቀበሌዎች በነዋሪዎችና በጸጥታ ሃይሎች መካከል አለመግባባት መፈጠሩን ከዜና ዝግጅት ክፍላችን ጋር ቃለምልልስን ያደረጉ እማኞች ገልጸዋል።
በዞኑ ስር በሚገኙ የማጎ ፓርክ አቅራቢያ በሃመር ወጣቶችና በጸጥታ ሃይሎች መካከል በተፈጠረው ግጭት አንድ የፖሊስ አባል ተገድሎ አራት ተጨማሪ አባላት ጉዳይ እንደደረሰባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል።
በነዋሪዎችና በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ በአንድ የፖሊስ ጣቢያ ላይ የመሳሪያ ዘረፋ እንደተፈጸመ የገለጹት እማኞች በጸጥታ አባላት ላይ ቅሬታን እያሰሙ ያሉ ነዋሪዎች አካባቢውን ተቆጣጥረው እንደሚገኙም አክለው ተናግረዋል።
የአስችኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ መድረግን ተከትሎ በዞኑ ስር የሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ቁጥራቸው በአግባቡ ሊታወቅ ያልቻለ ሰዎች ለእስር ተዳርገው እንደሚገኙም ታውቋል።
በደቡብ ኦሞ ዞን ስር በሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎች የመሬት ቅርምት ተካሄዷል በማለት ነዋሪዎች ከመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ መቆየታቸው ይታወሳል።
ይሁንና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ መደረግን ተከትሎ በዞኑ ከቀናት በፊት የተቀሰቀሰው ግጭት ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ነዋሪዎች ለኢሳት አስረድተዋል።
በአካባቢው ያለው ውጥረት ዕልባትን ባለማግኘቱ ምክንያት በጸጥታ ሃይሎች እየተፈጸመ ያለውን አፈናና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በአግባቡ ማወቅ እንዳልተቻለ ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ እማኞች አክለው ገልጸዋል።
ተመሳሳይ ችግሮች በተለያዩ የክልል ከተሞች በመፈጸም ላይ መሆናቸውን ነዋሪዎች ለመገናኛ ብዙሃን ሲገልጹ መቆየታቸውም ይታወቃል።