በደቡብ ኦሞ የረሃብ አድማ ከጀመሩ አራት የኅሊና እስረኞች መካከል አንደኛው ራሱን ስቶ ሆስፒታል ገባ

የካቲት ፳፫ ( ሃያ ሦስት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በደቡብ ኦሞ ዞን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ተይዘው ከነበሩት 10 የኅሊና እስረኞች ውስጥ ስድስቱ ከተፈቱ ሦስት ሳምንት በኋላ ከትናንት በስቲያ ሰኞ የረሃብ አድማ መጀመራቸው ከተዘገበ በሁዋላ፣ አቶ አባስ አብዱላሂ ራሱን በመሳቱ ሆስፒታል ተወስዶ ‹የህክምና ዕርዳታ ተደርጎለት መመለሱን የዓይን እማኞች ገለጸዋል ፡፡ የአቶ አባስን በጠኔ መውደቅ ተከትሎ የታሳሪ ቤተሰቦች በፖሊስ መምሪያ ኃላፊዎች ፊት ሲላቀሱ እንደነበር የአይን እማኞች ገልጸዋል።
ይህንኑ የረሃብ አድማ ተከትሎ ለ105 ቀናት በነዚህ እስረኞች ጉዳይ ግልጽ ምላሽ ያልሰጠው የዞኑ ኮማንድ ፖስት በኦቶ አባስ አብዱላሂና በወጣት ዳዊት ታመነ ላይ በጂንካ ከተማ ፍርድ ቤት በከተማው ዐቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶ የክስ ቻርጁም ደርሷቸዋል። አቶ ዘሪሁን ኢበዞ ላይምርመራ የተጀመረ ሲሆን፣ በሌላው እስረኛ በኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት ም/ል ሊቀመንበር መምህር ዓለማዬሁ መኮንን ላይ ምንም መረጃ ባለመገኘቱ ክስ ሊመሰረት ያለመቻሉን ምንጮች አሳውቀዋል፡፡
በወጣት ዳዊት ላይ የቀረበው ክስ ‹‹ የህዝብን ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር የወጣውን አስቸኳይ አዋጅ ቁጥር 984/2009 አንቀጽ 12/1 እና አስቸኳይ ጊዜ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 6 የተመለከተውን በመተላለፍ ›› የሚል ሲሆን ፣ ‹‹ ህዳር 5 ቀን 2009 ዓም ከጠዋቱ 12 ሰዓት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እና መመሪያ በሚጣረስ ሁኔታ …ህዝብን መንግስት ላይ ሊያነሳሳ የሚችል …. የሟች ሳሙኤል አወቀ ፎቶ ያለበትን … ጥቅሶች … ሁለት ጥቁር ቲ-ሸርት በቤቱ አስቀምጦ በብርበራ በመያዙ … ያልተፈቀደ አልባሳት መልበስ እና የህዝብን ሰላምና ጸጥታ ለማደፍረስ ድጋፍ ማድረግ ወንጀል ተከሷል፡፡ ›› የሚል ይገኝበታል።
በአቶ አባስ አብዱላሂ የክስ ቻርጅ ላይ የቀረበው ክስ ደግሞ “በኦሮሚያ ተነስቶ የነበረውን ሁከትና ብጥብጥ በመደገፍና ህዝብን የሚያነሳሳ ንግግር በመናገር መንግስት የኦሮሚያ ህዝብን በእሬቻ በዓል ላይ የአይሮፕላን ቦምብ በመጣል ህዝቡን ጨፈጨፈ በማለት እና አንድ የጦር መሳሪያ እና ቀለህ በማሳየትና ከስኳር ፕሮጀክት የጂንካ ህዝብ ምን ተጠቀማችሁ፣ ነዋሪው እየተንከራተተ ከሌላ ዞኖችና ክልሎች የመጡ ሰዎች ናቸው እየተቀጠሩ ያሉት በማለት በፈጸመው ሁከትና ብጥብጥ የሚያነሳሳ ቅስቀሳና መቻቻልንና አንድነትን የሚጎዳ ተግባር ወንጀል ተከሰዋል፡፡›› የሚል ነው።