በደቡብ ኦሞ ዞን ያንዣበበው የረሃብ አደጋ አሳሳቢ መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ

ታኅሣሥ ፳ (ሃያ)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በደቡብ ኦሞ ዞን  ቆላማ የአርብቶ አደር  አካባቢዎች  በተለይም  በሃመር፣ ኛንጋቶምና ዳሰነች  እንዲሁም ሳላማጎ ወረዳዎች የረሃብ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ዓለም አቀፍ ተቋማት ድምጻቸውን ማሰማት ከጀመሩ የቆዩ ቢሆንም፣ ምንም አይነት ቅድመ ዝግጅት ሳይደረግ ረሃብ መከሰቱን የአካባቢው ነዋሪዎችና የግብርና ባለሙያዎች ተናግረዋል።

በአሁኑ ጊዜ ረሃቡ ቅድመ ግምት በተሰጣቸው ቆላማ ወረዳዎች ሳይወሰን ወደ ወይና ደጋና ደጋ አርሶአደር አካባቢዎች እየተዛመተና በእጅጉ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ  ነው፡፡ የመንግስት ቴሌቪዥን ታህሳስ 19፣ 2009 ዓም የዜና እወጃው ‹‹ በኢልኒኖ የአፍሪካ ቆላማ አካባቢዎች በድርቅ የሚጠቁና ለረሃብ የሚጋለጡ ቢሆንም ኢትዮጵያ በድርቁ የሚመጣውን ችግር ለመቋቋም ትችላለች የሚል ዜና አቅርቧል።

የአካባቢው ነዋሪዎችና ባለሙያዎች ግን ቢያንስ በዞናቸው ድርቁን ለመቋቋም የተወሰደ አንድም እርምጃ የለም የለም ይላሉ። “ ረሃቡ በገሃድ እየታየ ነው፤ ይህን ተከትሎ የከፋ አደጋ እንዳይከሰት በእጅጉ እንሰጋለን” ሲሉ ፍርሃታቸውን ይገልጻሉ። በስኳር ፕሮጄክቶችና በግልገል ጊቤ 3 የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክት ምክንያት አርብቶ አደሩ በመናፈቀሉ፣ቀድሞ በኦሞ ወንዝ ዳር ጎርፍ- ሸሽ ደለል ላይ ይመረት የነበረው የእህል ምርት ተቋርጧል። ይህም አደጋውን የከፋ እንደሚያደርገው ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

የዞኑ የተለያዩ ሴክተር መ/ቤት ባለሙያዎች እንደሚገልጹት ከሆነ ‹‹ ከመንግስት የስኳርና የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በ‹ኢንቨስትመንት› ሥም የተያዘው ከ106 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትም ለችግሩ  መባባስ አስተዋጽኦ ያደርጋል። እንደባለሙያዎቹ  ገለጻ ‹‹ በኢንቨስትመንት ሥም በተወሰደው ቦታ ላይ አንድ ኩንታል እህል አልተመረተም። አርብቶ አደሮቹ ቦታውን ሳይነጠቁ እንደያዙት ቢቆዩ ኑሮ ቢያንስ ኑሮአቸውን ለመደጎም የሚያስችል ምርት ለማምረት ይችሉ ነበር።

በደቡብ ኦሞ ዞን ከህወሃት ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸው ‹‹ ኢንቨስተሮች ›› በወሰዱት ከ100 ሺ ሄክታር በላይ መሬት ከአስራ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ ከባንክ ተበድረውበት እና ከቀረጥ ነጻ እቃዎችን አስገብተውበት አንድም ምርት ሳያመርቱ ወይም መሬቱን ሳያለሙ ለአመታት መቀመጣቸው በዞኑ ውስጥ ትልቅ መነጋጋሪያ ርእስ ሆኖ እንደቀጠለ ነው። ቀድም ብሎ ባለሃብቶቹ መሬቱን በማስያዝ ወደ 1 ቢሊዮን ብር እንደተበደሩበት ኢሳት ዘግቦ የነበረ ቢሆንም፣ አዳዲስ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ግን ገንዘቡ ከ11 ቢሊዮን 100 ሺ ብር በላይ ነው።

ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች ለኢሳት እንደገለጹት፣ ‹‹ኢንቬስተሮቹ ›› ከዚህ የተዘረፈ መሬት ላይ ቦታውን በማዘጋጀት ሥም የግራር ዛፍ በመጨፍጨፍ፣ የከሰል  ምርት እያመርቱ ወደ አርባምንጭና አዲስ አበባ ሲጭኑ ቆይተዋል።  ባለሃብቶቹ  ካለፈው ዓመት ጀምሮ ደግሞ ከዞኑ መስተዳደር የተረከቡትን ‹ዶኮሞ ኦይል ፕኤልሲ/ Docommo  Oil PLC›› ለሚባል ኩባንያ አሳልፈው በመሸጥ፣  የአካባቢው ህዝብ ለባህል መድሃኒትነት የሚያገለግሉ ዛፎችን በመጨፍጨፍ ‹‹ኢሴንሺያል ኦይል ኦፍ አቢሲኒያ/ Essential Oil of Abyssinia/ የሚባል ለውበትና ሌላም ጥቅም የሚውል ምርት ለማምረት የደን ጭፍጨፋ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።