በደቡብ ኦሞ ዞን የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰራዊት ተሰማራ

መጋቢት ፲፪ (አሥራ ሁለት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በደቡብ ኦሞ ዞን የካይሳ እና አካባቢው ነዋሪዎች የወረዳ ይገባኛል ጥያቄ ማንሳታቸውን ተከትሎ በወረዳው እና በአካባቢው ከፍተኛ የሆነ ውጥረት ነግሷል። የነዋሪዎቹን ሕጋዊ ጥያቄዎች ሕጋዊ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ እስራት እና አፈና በማድረግ ወታደራዊ ሃይል እንዲሰፍር ተደርጓል።
በሳላማጎ፣ በና ጸማ እና ሃመር ወረዳዎች ሽፍታዎች አሉ በሚል ምክንያት በአርብቶ አደሮች ላይ ኦፕሬሽን በሚል ዘመቻ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጦር ሃይል እንዲዘምት በማድረግ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ነው። የነዋሪዎቹን ጥያቄዎች ምላሽ አለመሰጠቱ፣ አስቀድሞ ስለሚሰሩ ፕሮጀክቶች ነዋሪውን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች አለመሰራታቸውን ተከትሎ አርብቶ አደሩን አስቆጥቶታል። በዞኑ በቻይና መንገድ ስራ ድርጅት የተሰማሩ ኢንጅነሮች፣ ፎርማኖች እና ሌሎች ሰራተኞች ላይ ግድያ መፈጸሙን እና ወታደራዊ ሃይሉ በሚወስዳቸው እርምጃዎች ውጥረት እንዲፈጠር ማድረጉን ምንጮቻችን ገልጸዋል።