ኅዳር ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ በደቡብ ኢትዮጵያ በፓርቲ መሪዎች፣ በፓርቲ አባላት እና በህዝብ ላይ ወታደራዊ የኃይል እርምጃን ጨምሮ ከፍተኛ የሰብዐዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመ መሆኑን ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በደቡብ ኦሞ ዞን ጂንካ ከተማ ህዳር 5 /2009 ዓ.ም የኦሞ ህዝቦች ዲሞክርሲዊ ኅብረት/ ኦህዲኅ/ ምክትል ሊቀመንበርና የዞኑ ጽ/ቤት ተጠሪ መምህር ዓለማዬሁ መኮንን ፣ የዞኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ወጣት ዳዊት ታመነ ፣ እንዲሁም ቀድሞ የመኢአድና አንድነት የዞን ተጠሪ የነበሩት አቶ ስለሺ ጌታቸው ፣ ያለፍርድ ቤት ማዘዣ የእያንዳንዳቸው ቤት በአስራ አምስት ታጣቂ ኃይል አባላት ተበርብሮ ምንም ባይገኝም ለእስራት ተዳርገው እስካሁን በእስር ላይ ይገኛሉ።
ህዳር 06/ 2009 ዓም ደግሞ አቶ ዘሪይሁን ኤበዞ በተመሳሳይ መንገድ ተይዘው በጂንካ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ታስረዋል፡፡ ህዳር 8 ደግሞ የኦህዲኅ የዞን ጽ/ቤት ምክትል ተጠሪ መምህር ኢንዲሪስ መናን ከሥራ ቦታቸው ፣ እንዲሁም የዞኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ወጣት መሃመድ ጀማል የታሰሩትን ለመጠየቅ ፖሊስ ጣቢያ በሄደበት ወቅት እርሱ በሌለበት ቤቱ ተበርብሮ አንዳችም ነገር ሳይገኝ በዞኑ የደህንነት ኃላፊ አቶ አልዓዛር / በቅጽል ስሙ ‹ባቡሬ› / ትዕዛዝ በዚያው ለእስራት መዳረጉን ታውቋል።
መምህር ዓለማዬሁ መኮንንና መ/ር ኢንድሪስ መናን የጂንካ የመሰናዶ/ፕርፓራቶሪ ሁለተኛደረጃ ት/ቤት መምህራን ሲሆኑ፣ የዚህ ት/ቤት የሥራ ባልደረባ መምህር ሻመናም በፖሊስ ተይዞ እንደተለቀቀ ምንጮቹ አሳውቀዋል ፡፡ ሁኔታውን በቅርበት የሚከታተሉ ከተማው ነዋሪዎችና የታሳሪዎች ቤተሰቦች እንደሚገልጹት በከተማው እየሆነ ያለው በዞናቸው የተለመደ ቢሆንም፣ የአሁኑ ከመቼውም ጊዜ የከፋው ሲሆን ከከተማቸው የጸጥታና ደህንነት ሁኔታ ሲመዘን ይህ በመንግስት በኩል ለህዝብ ግልጽ ያልሆነ ከፍተኛ ሥጋት እንዳለ ያመለክታል።
በህወኃት አባላት የሚመራው ኮማንድ ፖስት ‹‹ እዚህ ዞን ችግር አለ ፤ እኛ አዋጁን ያወጣነው እናንተ በምትወስዱት ማንኛውም እርምጃ እንዳትጠየቁ ለማድረግ ነው፤ ሆኖም እናንተ ከማሰር ያለፈ እርምጃ ለመውሰድ አልቻላችሁም ፣በዚህም እስር ቤቶችን ሞላችሁ እንጂ ህዝቡን ከጥፋት አልመለሳችሁም ፤ ከዚህ በኋላ ተጨባጭ ጠንካራ እርምጃ ወስዳችሁ ካላሳያችሁን ፣እኛ ጠንካራ እርምጃ ምን ማለት እንደሆነ በእናንተ ላይ እርምጃ ወስደን እናሳያችኋለን›› በማለት ለማስፈራራት ቢሞክሩም ፣ የከተማው ፖሊሶች ‹‹ ምን አድርጉ ትሉናላችሁ፣ እናንተ ከሌላ ቦታ የመጣችሁ ናችሁ፣ እኛ ግን እዚሁ ተወልደን ያደግን የህዝቡ ልጆች ነን፣ ከዚህ በተጨማሪ ምንም ወንጀልና ጥፋት በሌለበት በህዝብ ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሙያችን ሥነ ምግባርና ኅሊናችን አይፈቅድልንም ፡፡ ከዚህ አልፎ እናንተ ነገ ትሄዳላችሁ፣ እኛ ግን ካሳደገን ህዝብ ጋር እንቀራለን፤ በህግ ባንጠየቅም ማን ላይ ፣ለምን ተኮሳችሁ የሚለውን ለቤተሰባችን፣ ለጎረቤቶችና ለህዝብ ማስረዳት ፣ለኅሊናችን ማሳመን ይጠበቅብናል ፡፡ ስለሆነም በህዝብ ላይ አግባብ ያልሆነ እርምጃ ከመውሰድ በእኛ ላይ ቢወሰድ ወይም ከሥራው ተባረን ህዝቡን ለምነን ብንበላ ይሻለናል›› በማለት መልስ መስጠታቸውን የዜናው ምንጮች ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በዞኑ ውስጥ ከከተማዋ ውጪ በአርብቶአደር ወረዳዎች በተለይ በበና ጸማይና ሃመር ወረዳዎች ወጣቶች እምቢታቸውን እየገለጹ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎ የመንግሥት ታጣቂ ኃሎች ይህን ተቃውሞ ለማፈን ለሚወስዱት የኃይል እርምጃ የአጸፋ መልስ መስጠት መጀመራቸውን የአካባቢው ምንጮች ይናገራሉ፡፡ የአጸፋ እርምጃው በተለይ በሃመር ወጣቶች ከጥር 2007 ዓ.ም የተጀመረና ለበርካታ ታጣቂ ፖሊሶች፣ መከላከያ ኃይልና ሲቪሎች ሞት ምክንያት ሲሆን ጥቃቱ ወደ በና ኩሌ ወረዳ ተሸጋግሮአል።
ባለፈው ወር በአንድ ቀን በሶስት የተለያዩ ቦታዎች ወጣቶች በወሰዱት እርምጃ በበና ጸማይ ወረዳ የአልዱባ ቀበሌ ፖሊስ ጣቢያ ሲፈርስ ፣ በሃመርና በና ጸማይ ወረዳዎች አዋሳኝ የቱሪስት መኪና በጥይት ተመትቷል። እንዲሁም ከማጎ ፓርክ አቅራቢያ በኩራዝ 2 ፕሮጀክት መታጠፊያ መንገድ ላይ አንድ ፖሊስ ሲገደል ሦስት ፖሊሶች ደግሞ ቆስለዋል።
የሃመር ወጣቶችን የተቃውሞ እንቅስቃሴ በሚመለከት ወጣቶቹ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ የተወካዮች ም/ቤት አባል ቀጥሎም ከ2007 ጀምሮ የዞኑ ም/አስተዳዳሪ የነበሩት የሃመር ተወላጁ አቶ አወቀ አይኬ ወጣቶችን እንዲያግባቡ በተላኩበት በመኪናቸው ላይ ተተኩሶ መስተዋቱ መመታቱን ፣ አብረው መኪና ውስጥ የነበሩ የሃመር ብሄረሰብ ተወላጅ በጥይት መቁሰላቸውም ይታወቃል፡፡ አቶ አወቀ አይኬ በቅርቡ በዞን ደረጃ በተደረገ ግምገማ ‹‹ እኔ አርጅቻለሁ፣ ማረፍ እፈልጋለሁ ›› ብለው ጡረታ ለመውጣት ጠይቀው ከሥልጣናቸው መልቀቃቸው፣ ከዚሁ የወጣቶች የተቃውሞ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ከጀርባ ግፊት ያለበት እንደሆነ ምንጮች አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የተማሩ የሃመር ተወላጆች የጥቃት ዒላማ የሆኑ ሲሆን፣ ለዚህም የቀድሞ የሃመር ወረዳ አስተዳዳሪና የዞኑ ም/አስተዳዳሪ ሆነው ያገለገሉት አሁን በመንግስት ሥራ ላይ ያልሆኑት አቶ በእምነት እና በዞኑ የተለያዩ መ/ቤቶች ያገለገሉትና አሁንም በሥራ ላይ ያሉት አቶ ዲለማ ጎዴ ፣ እንዲሁም የሃመር ወረዳ ፖሊስ አዛኝ በዚሁ ሳምንት ለእስር መዳረጋቸውን በማስረጃነት ያቀርባሉ፡፡ በእንደዚህ ዓይነቱ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ከዞኑ ዋና ከተማ ወደ ሃመርና ኩራዝ ወረዳ ዋና ከተሞች የሚወስደው መንገድ ፣እንዲሁም የኩራዝ ስኳር ፕሮጀክቶች ወደሚገኝበት ሳላ ማጎ ወረዳ የሚወስደው ዋናው መንገድ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በተደጋጋሚ መዘጋታቸውንና እንቅስቃሴ ተቋርጦ ቆይቷል።
ይህ 25 ዓመት ብሶት የወለደው ከህዝብ ውስጥ የወጣ ህዝባዊ ትግል ቢሆንም፣ የጂንካ ከተማ ነዋሪና በዞኑ በሰላማዊ መንገድ የሚታገለው ድርጅት/ ኦህዲኅ/ ባልዋሉበት የጥቃት ዒላማ መሆናቸው አነጋጋሪ ሆኗል። ከዓመት በላይ በዘለቀው የኮንሶ ህዝብ የማንነትና የአከላለል ጥያቄ ደግሞ፣ አገዛዙ ለህዝባዊ ጥያቄ ተገቢና ህጋዊ መልስ በመስጠት ፋንታ በሃይል ለማፈን የተለያዩ አሰቃቂ እርምጃዎችን የገጠርና ከተማ ነዋሪዎችን በተናጠልና ጅምላ በመግደል፣ በጅምላ በማሰር፣በገጠር ቀበሌዎች ቤቶችን /መንደሮችን በማቃጠል ንብረት በማውደምና ማሰደድ፣ በፍተሻ ሥም በመዝረፍ፣ የህዝብ ተወካዮችንና ባህላዊ መሪዎችን ወደ አርባምንጭ ወስደው በማሰር ፣ ለመንግስት ሠራተኞች ደመወዝ በመከልከል አስከፊ እርምጃዎችን መውሰዱን ቀጥሎበታል።
ባሳለፍነው ሳምንት በመቶዎች የሚቆጠሩ የኮንሶ ተወላጆች በመትረየስ በታገዘ ተኩስ ከቤትና ቀዬኣቸው በጅምላ እየታፈሱ ታስረዋል፡፡ በያዝነው ሣምንት በልዩ ወረዳው ዋና ከተማ -ካራት እና በ ጋቶ ከተማ መካከል በሚገኘው ጎጨጨ በሚባል የገጠር ከተማ ታጣቂ ኃይሎች ለገበያ በወጣው ህዝብ ላይ መትረየስ ተኩሰው 9 ሰዎች ሲቆስሉ አንዱ ህይወቱ አልፏል። በርካቶችም ታፍነው ተወስደዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ የኮንሶ የተማሩ ተወላጆችና ወጣቶች የጥቃት ዒላማ በመሆናቸውና ያለምንም ጥያቄ እንዲገደሉ ትዕዛዝ በመሰጠቱ ለመሰደድ መገደዳቸውን–በዚህም ወደ አርባምንጭና ጂንካ ሄደው ተደብቀው ለመኖር መገደዳቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
በተማሩ የኮንሶ ተወላጆች ላይ ግድያው ያነጣጠረ ስለመሆኑ በቅርቡ በልዩ ወረዳው አንድ ዶክተርና ባለቤታቸው መገደላቸውን በማስረጃነት ያቀርባሉ፡፡ ድርጊቱ “ የኮንሶን ህዝብ ከምድር ለማጥፋት የታቀደ ይመስላል” በማለት የአገር ሽማግሌዎች ሥጋታቸውን እየገለጹ ሲሆን፣ ይህ ሁኔታ በአስቸካይ ጊዜ አዋጁ እንደተደገፈና እንደተባባሰም ይናገራሉ፡፡
ህዝቡ ቤታቸው ተቃጥሎ ለተፈናቀሉ፣ የመንግስት ሰራተኛ ለነበሩ፣ ከሞት ለማትረፍ እንዲሰደዱ ያደረጋቸውን ልጆቹን መደጎም ይቅርና በዚህ ጭንቅ ውስጥም መሄጃ አጥቶ በቀዬው ያለው ህዝብ ከምርት ሥራ በመውጣቱ በበቂ መመገብ አልቻለምና ከወታደራዊ እርምጃው በተጨማሪ ህጻናትና አረጋዊያን በረሃብና በሽታ እየተሰቃዩ ሞታቸውን እየተጠባበቁ መሆኑን በምሬት እየገለጹ ነው።ይህን ዓይነት አረመኔና ጨካኝ አገዛዝ በእድሜ ዘመናችን አላየንም ሲሉ አምርረው አውግዘዋል።
“ጩሄታችንን የሚያሰሙልን፣ በደላችንን የሚገልጹልን ልጆቻችን አንድም ተገድለዋል፣ ወይም ታስረዋል ወይም ተሰደዋልና በአገር ቤትና ከአገር ውጪ ለሚገኙ ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ‹‹ ድምጻችንን ለወገኖቻችንና ለዓለም ህዝብ አሰሙልን፣ ከማለቃችን በፊት ድረሱልን፣ ይህ የአረመኔዎች ዘረኛ አገዛዝ እንዲወገድና የምንተርፈው የሥቃይ ቀናችን እንዲያጥር በኅብረት ቁሙ ›› በማለት ጥሪያቸውን አስተላለፈዋል፡፡