በደቡብ ኢትዮጵያ በስሎቫኪያና ቼክ ሪፐብሊክ ቱሪስቶች ላይ ጥቃት መፈጸሙ ተገለጸ

ኢሳት (ህዳር 5 ፥ 2009)

በደቡብ ክልል ሚዛን ከተማ አካባቢ በጉብኝት ላይ የነበሩ 10 የስሎቫኪያና የቼክ ሪፐብሊክ ቱሪስቶች ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች ዝርፊያ ተፈጽሞባቸው ሹፌራቸው መገልደሉ ተገለጸ።

የቼክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከቀናት በፊት በክልሉ ጉብኝት በማድረግ ላይ የነበሩት ቱሪስቶች በታጠቁ ሃይሎች ገንዘብን ጨምሮ የባንክ መገልገያ ካርዶችና ሌሎች ንብረቶቻቸው እንደተወሰደባቸው ሰኞ ይፋ አድርጓል።

የቼክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ የሆኑት ኢሬና ቫሌንቶባ፣ ዝርፊያ ከተፈጸመባቸው የቼክ ተወላጆች መካከል አንድ ሴት ጉዳት እንደደረሰባት ለሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

ቱሪስቶችን በማጓጓዝ ላይ የነበረ ማንነቱ ያልተገለጸ አንድ ሹፌር በተተኮሰበት ጥይት ጉዳት ደርሶበት ለህክምና ቢወሰድም ህይወቱ ማለፉን አሶሼይትድ ፕሬስ የቼክ ውጭ ጉዳይ ባለስልጣናትን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዙ የቱሪስቶች ቁጥር በከፍተኛ መጠን መቀነሱ ሲገለፅ ቢቆይም መንግስት ቱሪስቶች ያለምንም የደህንነት ስጋት ወደፈለጉት ስፍራ መጓዝ ይችላሉ ሲል ማስታወቁ ይታወሳል።

ይሁንና መንግስት ለቱሪስቶች ማረጋገጫን ቢሰጥም በአስሩ ቱሪስቶች ላይ በደቡብ ክልል ሚዛን ኣከባቢ የተፈጸመው ዝርፊያ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ታውቋል።

የስሎቫኪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ዝርፊያ የተፈጽሞባቸውን ስድስት የሃገሪቱ ዜጎችን ወደ ሃገራቸው መመለሱን አስታውቋል።

በኢትዮጵያ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ የስሎቫኪያ መንግስት ዜጎቹ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ አሳስቦ እንደነበር ታሰር የተሰኘ የሃገሪቱ የመገናኛ ተቋም ሰኞ ዘግቧል።

በአለም አቀፍ ቱሪስቶች ላይ የተፈጸመውን ዘረፋና የሹፌሩን ግድያ በተመለከተ የክልሉም ሆነ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እስካሁን ድረስ የሰጡት ምላሽ የለም።

በርካታ የብሪታኒያ አስጎብኚ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ተግባራዊ ተደርጎ ያለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት በማድረግ ወደ ሃገሪቱ ሊያደርጉ የነበሩ ጉብኝቶች እንዲሰርዙ ማድረጋቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን ባለፉት ሶስት ወራቶች ብቻ ከቱሪስት ገቢ ሰባት ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ መታየቱን ሰሞኑን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በአስሩ ቱሪስቶች ላይ የተፈጸመው ዝርፊያ በጎብኚዎች ላይ ስጋትን ያሳድራል ተብሎ ተሰግቷል።