(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 14 /2010)
መሳሪያ ያነገቡና የተደራጁ ታጣቂዎች ዛሬ ማለዳ የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ጣቢያን በመውረር መኮንኖችን ጨምሮ 5 ፖሊሶችን መግደላቸው ታወቀ።
የደቡብ አፍሪካ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው በምሥራቃዊ ኬፕ ግዛት በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ዛሬ በደረሰው በዚህ ጥቃት ሦስቱ ፖሊሶች ወዲያውኑ መሞታቸው ታውቋል።
ሁለቱ ፖሊሶች ደግሞ ታግተው ከተወሠዱ በኃላ 4 ማይል ርቀት ላይ አስከሬናቸው ተገኝቷል፡፡
አላማቸውና ማንነታቸው ያልታወቀው ታጣቂዎች ከፖሊስ ጣቢያው 10 ጠመንጃዎችን እንደሁም ፖሊሶች የሚገለገሉበትን ቫን ተሽከርካሪ መውሰዳቸው ታውቋል።
ፖሊስ ጣቢያውን ከማጥቃታቸው አስቀድሞ በአካባቢው የተካሔደው የገንዘብ ዘረፋ በዚሁ የተደራጀ ቡድን ሳይፈጸም እንዳልቀረም ተመልክቷል።
የደቡብ ኦፍሪካ ብሔራዊ ፖሊስ ኮሚሽን አዛዥ ጄኔራል ኬሔላ ጆን ሴቶል ገዳዮቹ ከሕግ እንደማያመልጡ ቃል ገብተዋል፡፡