በደቡብ አፍሪካ 10 ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ስር ዋሉ

ኢሳት (ግንቦት 10 ፥ 2008)

የደቡብ አፍሪካ የጸጥታ ሃይሎች ምንም አይነት የጉዞ ሰነድ ሳይዙ ወደሃገሪቱ ገብተዋል የተባሉ አስር ኢትዮጵያውያንን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ገለጡ።

ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ሃገራትን በማቋረጥ ወደ ሃገሪቱ የገቡ መሆናቸውንና ከቀናት በኋላም ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ የደቡብ አፍሪካ መገናኛ ብዙሃን ፖሊስን ዋቢ በማድረግ ሃሙስ ዘግበዋል።

በቅርቡ የዛምቢያ መንግስት ሃገሪቱን ተጠቅመው ወደ ደቡብ አፍሪካ ሊያቀኑ ነበሩ ያላቸውን ከ40 በላይ ኢትዮጵያውያንን በቁጥጥር ስር አውሎ የሶስት ወር የእስር ቅጣት ማስተላለፉ ይታወሳል።

የአለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ አለም አቀፍ አካላት ከኢትዮጵያ በመሰደድ ላይ ያሉ ሰዎች ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጨመረ መምጣቱን ይገልጻሉ።

የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ በቅርቡ በተመሳሳይ ሁኔታ ወደ ሃገሪቱ ገብተዋል የተባሉ ከ10 በላይ ኢትዮጵያውያን በምስራቃዊ የሃገሪቱ የሃገሪቱ ግዛት አካባቢ በምትገኘው የጀርምስተን ከተማ በቁጥጥር ስር ማዋላቸው ይታወሳል።

በተለያዩ ጊዜያት ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት በማቅናት ላይ የነቨሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን በማላዊ ናሚቢያና ታንዛኒያ ለእስር ተዳርገው የወራት የእስር ቅጣት ተላልፎባቸው እንደሚገኝም ለመረዳት ተችሏል።