በደቡብ አፍሪካ ታግተው የተወሰዱ ሁለት ኢትዮጵያዊያን ለጥቂት ከሞት ተረፉ

ጥቅምት ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ባለፈው ዓመት በደቡብ አፍሪካ በአስከፊ ሁኔታ በስደተኞች ላይ ያነጣጠረው ግድያና ዝርፊያ ድጋሜ የማገርሸት አዝማሚያው ምልክቶች ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ እየታየ ሲሆን፣ በቀድሞዋ ዋና ከተማ ጆሃንስበርግ ውስጥ ታግተው የተወሰዱ ሁለት ኢትዮጵያዊያን በፖሊስ ጣልቃገብነት ለጥቂት ከሞት ተርፈዋል።
የግል ሱቅ በመክፈት ሥራ የሚተዳደረው ፈይሳ ሊሬና ጓደኛው በሁለት አጋቾች ከስራ ቦታቸው ታግተው ከከተማ ውጪ ከተወሰዱ በኋላ ሊገድሏቸው እንደወሰኑ ፓሊስ በስፋራው ደርሶ እንዳስጣላቸው ፈይሳ ሊሬ ተናግሯል። ”አጋቾቹ እንዳሉኝ ከሆነ ለአምስት ጊዜያት ልንዘርፍህ ሞክረን ነበር አልተሳካልንም አሁን ግን እንገልሃለን ብለውኛል። ” ያለ ሲሆን፣ የአሁኑ ግን የመጨረሻ ውሳኔያቸው መሆኑን አጋቾቹ እንዳስረዱት የቤተሰብ አስተዳዳሪና የ5 ዓመት ልጅ አባት መሆኑንም ጨምሮ አስረድቷል።
አጋቾቹ ከፖሊስ ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርገው አንዱ ወዲያውኑ ሲገደል ሌላና ቆስሎ ማምለጡንና ፖሊስ ክትትሉን መቀጠሉን ኒውስ ቲዎንቲ ፎር ዘግቧል።