በደቡብ ሱዳን ጦርነቱ ቀጥሏል

ጥር ፱ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የውጭ የመገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት በአዲስ አበባ ሁለቱን ተፋላሚ ሃይሎች ለማስማማት ውይይት ቢጀመርም፣ በመሬት ላይ እየተደረገ ያለውን ጦርነት ለማስቆም አልተቻለም።

በዩጋንዳ መንግስት የሚደገፈው የመንግስት ጦር ቦር እየተባለ የሚጠራውን ስትራቴጂክ ከተማ ከተቆጣጠረ በሁዋላ በቅርቡ የተነጠቀውን ማላካልን መልሶ ለመያዝ ከፍተኛ ትግል እያደረገ ነው። መንግስት ከተማዋን መልሶ መያዙን ቢያስታውቅም፣ አማጽያኑ ግን ከተማዋ አሁንም በቁጥጥራቸው ስር እንደምትገኝ እየገለጹ ነው። ማላካል አብዛኛው የአገሪቱ ነዳጅ የሚመረትበት የአፐር ናይል ግዛት መግቢያ ነች።

ከ500 ሺ በላይ ህዝብ በተፈናቀለበት ጦርነት፣ የውጭ ሃይሎች ጣልቃ መግባታቸው ችግሩን እያወሳሰበው ነው። ምእራባውያን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የአሰሩዋቸውን ተቀናቃኞች እንዲፈቱ  ጫና እያሳደሩ ሲሆን፣ ኡጋንዳ ደግሞ በግልጽ ጦሩዋን በመላክ ድጋፉዋን ለሳልቫኪር መንግስት ገልጻለች።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሁለቱም ሃይሎች ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መፈጸማቸውን የገለጸ ሲሆን፣ ምናልባትም በጦርነቱ ውስጥ እየተሳተፉ ያሉ የሁለቱም ተፋላሚ ሃይሎች አዛዦች በአለማቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት እንዲከሰሱ ሁኔታዎችን ሊያመቻች ይችላል።