ታህሳስ ፯(ሰባት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ተሞክሮ የነበረው መፈንቅለ መንግስት መክሸፉን በተናገሩ ማግስት ግጭት መነሳቱን ረዩተርስ ዘግቧል። አልፎ አልፎ ይሰማ የነበረው ተኩስ በተከታታይ መሰማቱን የገለጸው ረዩተርስ፣ የአሜሪካ ልዩ ልኡክ የሆኑት ዶናልድ ቡዝ ሁኔታው ውጥረት የበዛበትና ያልተረጋጋ መሆኑን ገልጸዋል።
እስካሁን ባለው መረጃ 26 ሰዎች እንደተገደሉ ቢታወቅም አንዳንድ የመገናኛ ብዙሀን ከ60 በላይ ወታደሮች እንደተገደሉ እየዘቡ ነው። ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር የቀድሞው ምክትላቸው ስልጣን ለመያዝ ሲሉ የጀመሩት አመጽ ነው ይላሉ።
በርካታ ዜጎች በየኢምባሲዎች ተጠልለው እንደሚገኙ ታውቋል። በአገሪቱ የሚገኙ ከ50 ሺ ያላነሱ ኢትዮጵያውያንን እጣ ፋንታ በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን ያለው ነገር የለም።