በደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዳይሆነ አድርገዋል በተባሉት አካላት ላይ ማዕቀብ እንዲጣል አሜሪካ ጥሪ አደረገች

ኢሳት (ኅዳር 9 ፥ 2009)

አሜሪካ በደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዳይሆን አስተዋጽዖ አድርገዋል በተባሉ አካላት ላይ የተባባሩት መንግስታት ድርጅት የተለያዩ ማዕቀቦችን እንዲጥል ጥረት እያደረገች መሆኗን ገለጠች።

ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት የደቡብ ሱዳን መንግስትና በሪክ ማቻር የሚመራው የአማጺ ቡድን ስምምነት እንዲደርሱ ቢደረጉም ሁለቱ ወገኖች ዳግም ወደ ግጭት  መግባታቸው ይታወቃል።

በደቡብ ሱዳን መንግስትና በአማጺ ቡድኑ መካከል በአዲስ መልክ የተቀሰቀሰውን ግጭትና አለመግባባት ተከትሎ ኢትዮጵያ የአማጺ ቡድን መሪ ሪክ ማቻር ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ እገዳ መጣሏ ይታወሳል።

ይሁንና ሁለቱ ወገኖች ስምምነት እንዲደርሱ ግፊትን ስታደርግ ቆይታለች የምትባለው አሜሪካ ማቻር በደቡብ ሱዳን መንግስት ውስጥ ድርሻ እንዲኖራቸው ፍላጎት እንዳላት ትገልጻለች።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ሳማንታ ፓወር ሃገራቸው በደቡብ ሱዳን የተደረሰው ስምምነት ተግባራዊ እንዳይሆን አስተዋጽኦ ባደረጉ አካላት ላይ ማዕቀብ እንዲጣል በቀጣዮቹ ቀናት የውሳኔ ሃሳብ እንደምታቀርብ ለጸጥታው ምክር ቤት አባላት ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዲወስድ የሚጠበቀው ማዕቀብ የተለያዩ አመራሮችና ግለሰቦች ያካተተ እንደሚሆን አምባሳደሯ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት በመቆጠብ ከምክር ቤቱ አባላቱ አክለው አስረድተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይወስደዋል ተብሎ የሚጠበቀው ማዕቀብ በአዲሲቷ ሃገር ያለው ግጭት ዕልባት እንዲያገኝ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አምባሳደሯ አክለው አስታውቀዋል።

ይሁንና ሩሲያና ቻይና በአሜሪካ አነሳሽነት ተግባራዊ እንዲደረግ የታሰበው ማዕቀብ ሊቃወሙ ይችላሉ ተብሎ የተሰጋ ሲሆን ሁለቱ ሃገራት ማዕቀቡ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም ሲሉ አቋማቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።

የመሳሪያ ዝውውር እገዳና የአመራሮችን የባንክ ሂሳብ መዝጋት በማዕቀቡ ውስጥ ይካተታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዲፕሎማቶች ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የደቡብ ሱዳን ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ጆሴፍ ማሎክ በበኩላቸው የጸጥታው  ምክር ቤት እንዲወስድ የሚፈልገው ማዕቀብ የሃገራቸውን ሉዓላዊነት የሚጋፋ እንደሆነ ገልጸዋል።

በምስራቅ አፍሪካ አደራዳሪነት ስምምነት የደረሱት የደቡብ ሱዳን መንግስትና አማጺ ቡድኑ የጋራ ብሄራዊ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ባደረጉት ስምምነት መሰረት ሪክ ማቻር ወደጎረቤት ሱዳን ተሰደው የሚገኙ ሲሆን፣ ፕሬዚደንት ሳል ባኪር ከአማጺ ቡድኑ አፈንግጠዋል የተባሉ አመራርን በምክትል ፕሬዚደንትነት ሾመዋል።