ኢሳት (ሚያዚያ 17 ፥ 2008)
ኢትዮጵያ ከ10 ቀን በፊት በጋምቤላ የተጠለፉባትን ከ108 በላይ ህጻናትን ለማስመለስና ከ 208 በላይ በግፍ የተጨፈጨፉት ዜጎቿን ለመበቀል በታጠቁ የሙልሌ ጎሳ ሃይሎች ላይ እርምጃ እንዳትወስድ በደቡብ ሱዳን የሲቪል ማህበረሰብ አባላት በመጠየቅ፣ የተጠለፉት ህጻናትም በድርድር ሊመለሱ ይችላሉ በማለት የተማፅኖ ደብዳቤ ጻፉ።
የሙርሌ ብሄረሰብ በሚኖርበት በፒቦር አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ሶስት የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች እንዳስታወቁት፣ በታጠቁ ሙርሌ ሃይሎች የተወሰደውን አሰቃቂ የጅምላ ግድያ እርምጃ በፅኑ በማውገዝ፣ የኢትዮጵያ መንግስት የተጠለፉትን ህጻናትን ለማስመለስ ወታደራዊ እርምጃ ቢወስድ ወደ ሌላ አለመረጋጋት ከመምራቱም ባሻገር፣ የሴቶችንና የህጻናትን ህይወት በከፍተኛ ሁኔታ ሊቀጥፍ ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
Peace Communication Association, Stop Poverty Communal Initiative እና Agenda for Growth Organization የተባሉትና በደቡብ ሱዳን በፒቦር ግዛት የሚንቀሳቀሱት የሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች በጋራ ፊርማ ባወጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ የኢትዮጵያ መንግስት ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ከደቡብ ሱዳን መንግስትና ከቦማ ክልላዊ ግዛት ጋር መነጋገር ይኖርበታል። ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ብሄራዊ መንግስትና ከቦማ መንግስት ጋር ንግግር ማድረጓ የተጠለፉትን ህጻናት “በሰላም” ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ ዕድል ከፍተኛ ይሆናል ሲል ሬዲዮ ታማዙጂ የሚባል በሱዳን ጉዳይ ላይ የሚዘግበው ሬዲዮ ጣቢያ ገልጿል።
የድርጅቶቹ መሪዎች በጋራ ባወጡት በዚሁ መግለጫ፣ የደቡብ ሱዳን ብሄራዊ መንግስት ከቦማ ክልላዊ ግዛት ጋር በመተባበር በቅርቡ በጋምቤላ ክልል ወላጆቻቸው በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለው የተጠለፉትን ህጻናትን የማስመለስ ስራ መሰራት አለበት ብለዋል ሲል ሬዲዮው አክሎ ገልጿል። ለተጎዱ ቤተሰቦችም የደቡብ ሱዳን መንግስት ካሳ እንዲከፍል ለደቡብ ሱዳን ጥሪ አቅርበዋል ተብሏል።
የኢትዮጵያ መንግስት በደቡብ ሱዳን ገብቶ ጥቃት ቢያደርስ፣ በደቡብ ሱዳን ቋፍ ላይ ያለው የጸጥታ ሁኔታ አስከፊ ደረጃ ሊያደርሰው እንደሚችል ጋዜጣው ትንታኔ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው በሰጠው መግለጫ፣ ከጋምቤላ የተጠለፉ ህጻናት ያሉበትን ቦታ ለይቻለሁ በአጭር ጊዜ ጥቃት ከፍቼ ህጻናትን አስለቅቃለሁ ሲል እንደነበር ይታወሳል። የኢትዮጵያ መንግስት የመከላከያ ሰራዊቱ ደቡብ ሱዳን ገብቷል እያለ በመንግስት መገኛና ብዙሃን ሲያስወራ ቢቆይም፣ በጥቃቱ እስካሁን ድረስ ያስለቀቀው ከእገታ ያስለቀቀው ሰው የለም።