ጥቅምት ፳፫ (ሃያ ሦስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ዘጋርዲያን እንደዘገበው ዋና አዝዡ የተባረሩት በመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሀፊ በባንኪ ሙን ውሳኔ ነው።
ለመባረራቸው ምክንያት የሆነውም በጁባ ባለፈው በጋ የእርስበርስ ግጭት በተቀሰቀሰበት ወቅት ሰላም አስከባሪው ኃይል የሲቪሎችን ደህንነት ለመጠበቅ የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣት እንዳልቻለ ሪፖርት በመቅረቡ ነው።
የመንግስታቱ ድርጅት የደቡብ ሱዳን ግጭት ልዩ መርማሪ ቡድን ባደረገው ማጣራት እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ባለፈው ሀምሌ 8 እና 11 መካከል በመዲናዋ ጁባ በተቀሰቀሰው ግጭት በሌተናል ጄነራል ጆንሰን ሞጎአ ኪማኒ ኦንዲየኪ የአመራር እጥረት ሳቢያ ችግር መከሰቱን እንደደረሰበት በሪፖርቱ አስፍሯል።
በወቅቱ የረዴት ሰራተኞች በሆቴል ቅጥር ግቢ ተከበው ለጥቃት በተጋለጡበት ወቅት የሰላም አስጠባቂ ኃይል አባላቱ ድጋፍ ማድረግ ሳይችሉ መቅረታቸውን የአጣሪ ቡድኑ በሪፖርቱ ጠቁሟል።
በፕሬዚዳንት ሳልቫኪር እና በምክትላቸው ሪክ ማቻር ግጭት ከተቀሰቀሰበት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2013 ጀምሮ የመንግስታቱ ድርጅት የደቡብ ሱዳን ልዩ መልዕክተኛ በሀገሪቱ 16 ሺህ የሰላም አስጠባቂ ኃይል አሰማርቶ ይገኛል።
አሁን የተባረሩት ኬንያዊው የጦር አዛዥ ሌተናል ጀነራል ጆንሰን ሞጎአ ፤የደቡብ ሱዳን ሰላም አስጠባቂ ኃይል ሆነው በባንኪ ሙን የተሾሙት ባለፈው ግንቦት ነበር።