በደቡብ ሱዳን ችግር ዙሪያ የተጀመረው ድርድር ቀጥሎአል

የካቲት ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአዲስ አበባ በሚካሄደው ድርድር በቅርቡ ከእስር የተፈቱት 7ቱ የቀድሞ ከፍተኛ ባለስልጣናት ተሳታፊዎች ሆነዋል። ይሁን እንጅ ባለስልጣኖቹ ከሁለቱም ወገኖች ሳይሆኑ በገለልተኛነት በድርደሩ ላይ መገኘታቸውን ተናግረዋል። ገለልተኝነትን የመረጡበትም ምክንያት ሲናገሩ ደግሞ የጦር መሳሪያ የለንም የሚል ነው። የሳልቫኪር መንግስት ባለስልጣኖችን ያሰረው ከተቃዋሚው መሪ ሪክ ማቻር ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ነበር።

በሌላ በኩል ዩጋንዳ ጦሩዋን ከደቡብ ሱዳን ለማስወጣት እያንገራገረች ነው። አሜሪካ የዩጋንዳ ጦር አገሪቱን ለቆ እንዲወጣ ብትጠይቅም፣ የዩጋንዳ መንግስት ግን የደቡብ ሱዳን የሰላም ሁኔታ አስተማማኝ ባለመሆኑ ለመውጣት ፈቃደኛ አይደሉም ብሎአል። መውጣት ካለብን በሂደት መሆን አለበት ሲሉ አንድ የዩጋንዳ መንግስት የመከላከያ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።