ኢሳት (ኅዳር 23 ፥ 2009)
በደቡብ ምስራቃዊ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተከሰተውን አዲስ የድርቅ አደጋ ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ እንስሳት መሞታቸውንና ድርጊቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ስጋት ውስጥ እንደከተተ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ።
በአካባቢው በተከሰተው ድርቅ ምክንያት በርካታ አርብቶና አርሶ አደሮች እንስሶቻቸውን በድርቁ እንዳይሞቱ በመስጋት ለሽያጭ እያቀረቡ መሆኑንም የአለም ምግብ ፕሮግራም (FAO) በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው ሪፖርት ገልጿል።
የአካባቢው ነዋሪዎች እንደ ንብረት የሚቆጥሩትን የእንስሳት ሃብታቸውን ለገበያ በማቅረብ ላይ ቢሆኑም ገዢ በማጣታቸው ሳቢያ እንስሶቹ እየሞቱ መሆናቸው ታውቋል።
በአሁኑ ወቅት ባለፈው አመት በተከተሰተው የድርቅ አደጋ ምክንያት 9.7 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ለምግብ እጥረት ተጋልጠው የሚገኙ ሲሆን፣ በደቡብ ምስራቃዊ የሃገሪቱ አካባቢዎች የተከሰተው አዲስ የድርቅ አደጋ የተረጂዎችን ቁጥር ከፍ ያደርገዋል ተብሎ ተሰግቷል።
በአካባቢው ከጥቅምት ወር እስከ ታህሳስ ወር ድረስ መጣል የነበረበት ዝናብ በበቂ ሁኔታ ባለመጣሉ ሳቢያ በበርካታ ዞኖች አዲስ የድርቅ አደጋ ሊከሰት መቻሉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
በተለይ በምስራቅ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሶማሊ፣ ትግራይና የደቡብ አፋር ስራዎች አዲስ የተከሰተው የድርቅ አደጋ የከፋ የምግብ እጥረት ማሳደሩን ከድርጅቱ ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል።
በአምስት ክልሎች ውስጥ በሚገኙ በርካታ ዞኖች ተከስቶ የሚገኘው ይኸው የድርቁ አደጋ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት አደጋ ውስጥ እንዲገባ ማድረጉም ተገልጿል።
አለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ ተቋማት በበኩላቸው ድርቁ በሰው ህይወት ላይ ተፅዕኖን ከማሳደሩ በፊት አፋጣኝ ርብርብ መካሄድ እንዳለበት በማሳሰብ ላይ ሲሆኑ የክልሎቹም ሆነ የፌዴራል መንግስት አዲስ በተከሰተው የድርቅ አደጋ ዙሪያ እስካሁን ድረስ የሰጡት ምላሽ የለም።
ባለፈው አመት በተመሳሳይ መልኩ በስድስት ክልሎች የድርቅ አደጋ ተከስቶ ከ10 ሚሊዮን የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን ለአስቸኳይ የምግብ እጥረት ተጋልጠው ቆይተዋል።
የተረጂዎች ቁጥር ባለፉት ወራት በግማሽ ሚሊዮን አካባቢ ብቻ በመቀነሱ አሁንም ድረስ 9.78 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ እጥረት ውስጥ መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በመግለጽ ላይ ነው።