(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 28/2010) በደሴ ከተማ ዛሬ የስራ ማቆም መደረጉ ተገለጸ።
በነጋዴዎች የተመታው የስራ ማቆም አድማ ባለፈው ዓመት ከተጣለው ዓመታዊ የቀን ግብር ጋር የተያያዘ ነው።
በሌላ በኩል ዝዋይ በሚገኘው የካስትል ቢራ ፋብሪካ የሚሰሩ በሺህ የሚቆጠሩ ሰራተኞች የስራ ማቆም ከመቱ 10 ቀናት እንደሆናቸው ተገልጿል።
በሀዋሳ የኢንዱስትሪ መንደር የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ሰራተኞችም ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የስራ ማቆም አድማ መምታታቸው ታውቋል።
በደሴ ከተማ ከአቅም በላይ የተጣለው የገቢ ግብርን በመቃወም በተካሄደው በዚሁ የስራ ማቆም አድማ ከ1ሺህ በላይ የንግድ ቤቶች በራቸውን ዘግተው መዋላቸው ታውቋል።
የተጣለባቸውን ግብር በተመለከተ ይግባኝ ያሉት ነጋዴዎቹ ሰሞኑን ውሳኔ መሰጠቱን ተከትሎ አድማ መጥራታቸውን ነው የኢሳት ምንጮች የገለጹት።
አነስተኛው አመታዊ ግብር 100ሺህ ብር ሲሆን ከፍተኛው ሩብ ሚሊየን እንደሚደረስ ታውቋል።
የደሴ ነጋዴዎች ያለአቅማችን የተጣለውን ግብር አንከፍልም በማለት እያደረጉ ያሉትን አድማ ለማስቆም የመንግስት ባለስልጣናት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው ተገልጿል። የተዘጉትን ማሸግ መጀመሩንም ለማወቅ ተችሏል።
በሌላ በኩል የቢጂ አይ እህት ኩባንያ የሆነውና በዝዋይ የሚገኘው የካስትል ቢራ ፋብሪካ ሰራተኞች ለ10 ቀናት የዘለቀ የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸው ታወቋል።
ፎርቹን የተሰኘው የእንግሊዘኛ ጋዜጣ እንደዘገበው ከ1220 ሰራተኞች በላይ የተሳተፉበት የስራ ማቆም አድማ የተደረገው ከደሞዝ ጋር በተያያዘና በሌሎች ተጓዳኝ ምክንያቶች ነው።
ላለፉት ሶስት ዓመታት የደሞዝ ጭማሪ፣ የተለያዩ ጥቅማጥቅሞችና የደረጃ እድገት በአግባቡ እንዲፈጸምልን ጠይቀን ምላሽ ባለማግኘታችን አድማውን አድርገናል ማለታቸውን ጋዜጣው ገልጿል።
ባለፈው ሳምንት ሰኞ የተጀመረው የስራ ማቆም አድማ 4 የፋብሪካው አመራሮች ከሃላፊነት እንዲነሱ በማድረግ ለማስቆም የተሞከረ ቢሆንም የሰራተኞቹ ጥያቄ ባለመመለሱ መቀጠሉን ለማወቅ ተችሏል።
ፋብሪካው ከ15 እስከ 70 በመቶ የደሞዝ ማስተካካያ ለማደረግ ቃል በመግባቱ ሰራተኞቹ ለጊዜው ስራ ለመጀመር የተሰማሙ ቢሆንም ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ስራ መጀመራቸው አልተረጋገጠም።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በሀዋሳ የኢንዱስትሪ መንደር በጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች የሚሰሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች ባለፈው ሳምንት የስራ ማቆም አድማ ማደረጋቸውና እስከዚህኛው ሳምንት ድረስ በሰራተኛውና በፋብሪካዎቹ መካከል ስምምነት ሳይደረስ መቆየቱን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
ሰራተኞቹ እየናረ ከመጣው የኑሮ ውድነት ጋር በተያያዘ ፋብሪካዎቹ የሚከፍሏቸው ደሞዝ አነስተኛ መሆኑን በመግለጽ በተደጋጋሚ ተቃውሞ ቢያቀርቡም ‘’ከፈለጋችሁ ለቃችሁ መሄድ ትችላላችሁ። ከእናንተ የተሻሉ ብዙዎችን እናመጣለን የሚል የንቀት መልስ እንደሚሰጣቸው አንድ ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀ የፋብሪካው ሰራተኛ ለኢሳት ገልጿል።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ተጀምሮ የነበረውን የስራ ማቆም አድማ ለመቀልበስ የፋብሪካዎቹ ባለቤቶች ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ሆነው የጠሩት ስብሰባ ያለስምምነት መጠናቀቁንም ለማወቅ ተችሏል።