ሐምሌ ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኤግዚቢሸኑ ዜና በኢቲቪ ከተዘገበ በኃላ እንዳይተላለፍ የታገደው ያለፈውን ሥርዓት የሚያንቆለጻጽስ ነው በሚል ነው፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በእስክንድር በጎሲያን ሥነ ጥበባት ኮሌጅ ሥር የሚገኘው ትምህርት ቤት ከ1967 እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ ተማሪዎቹ ከሠሯቸው ልዩ ልዩ ሥዕሎች መካከል የተመረጣቸውን ሥዕሎች በሰኔ ወር መጀመሪያ ጀምሮ ለእይታ አብቅቷል፡፡
ዝግጅቱን አስመልክቶ የተዘጋጀው ካታሎግ በደርግ ዘመን የመጀመርያዎቹ ዓመታት የሥዕል ትምህርት ቤቱ ከነበረው መመርያና የደርግ መንግሥት ከሚከተለው ማርክሳዊ ርዕዮት ምን ይመስል እንደነበር ለማስቃኘት ያለመ ነው፡፡ በወቅቱ የነበረው ሥነ ጥበብ የወዝአደሩን ትግል፣ አርበኝነትን፣ የአብዮቱን ጀግኖችና የሠራዊቱን እናት አገርን የመጠበቅ ተጋድሎ እንዲያንፀባርቅ ይጠበቅ የነበረ ሲሆን በወቅቱ የነበሩት ሠዓሊያን ግን ሁኔታውን በምን መልኩ ይገልጹት
እንደነበር ያሳያል፡፡
ብዙዎቹ ሠዓሊያን በወቅቱ የነበረውን ርዕዮተ ዓለም በጥበባዊ ሥራቸው ላለማካተት ሲሉ አብዛኛዎቹ ከማርክሲስት ሌኒንስት ርዕዮተ ኣለም ይልቅ የታሪክ ባለውለታዎችን ወደማቅረቡ አዘንብለው እንደነበር የቀረቡት ሥራዎች ያሳያሉ፡፡
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮቻችን ስለጉዳዩ ተጠይቀው “የቀረቡት ሥራዎች ደርግን የሚክቡ አይደሉም፡፡እንዲያውም የሥነጥበብ ባለሙያዎች ጥበብን ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ እንዳትውል ያደረጉትን ተጋድሎ የሚያሳይ ነው፡፡ኢቴቪ ለምን እንዳይተላለፍ እንዳገደው ግልጽ አይደለም” ብለዋል፡፡
ኤግዚቢሸኑ በኢቴቪ እንዳይተላለፍ መታገዱ የሥዕል ት/ቤቱ አመራሮች ከሰሙ በኃላ ኤግዚቢሸኑን ለማሰተዋወቅ በር ላይ ሰቅለውት የነበረውን ባነር እንዲነሳ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide