በደራ ወረዳ የተፈጸመው ኢሰብዓዊ ድርጊት አነጋጋሪነቱ ቀጥሎአል -የወንጀሉ ተባባሪዎች የሆኑ 3 ፖሊሶች እስካሁን አልተያዙም

ህዳር ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን በደራ ወረዳ በገብሮ ቀበሌ የፍትህና ጸጥታ ሹም የሆነ ግለሰብ ከሶስት ፖሊሶች ጋር በመ ሆን በቀበሌው የሚኖርን አንድን ግለሰብ መሳሪያ ደብቀሀል በሚል ሰበብ ግለሰቡንና ባለቤታቸውን ልብሳቸውን በማስወለቅ እርቃናቸውን እንዲታሰሩ ማድረጉን፣ እንዲሁም ባልየው ብልቱ በገመድ እንዲታሰር ከተደረገ በሁዋላ ህዝብ በተሰበሰበበት አደባባይ እርቃኑዋን የሆነቸው ባለቤቱ አስጸያፊ ድርጊቶችን እንድትፈጽም፣ በሰደፍ በመመታቱዋም የስድስት ወር ልጇን እንድታስወርድ መደረጉን የገበሮን የቀበሌ ሊቀመንበር፣ የወረዳውን አስተዳዳሪና አንድ የምክር ቤት አባልን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል።

 

ዜናው በኢሳት ይፋ ከሆነ በሁዋላ ኢትዮጵያውያን የተሰማቸውን ስሜት እየገለጹ ነው። አንድ በደቡብ ክልል ተወላጅ የሆኑ ሰው በአካባቢያቸው በደራ ከተፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰት ያለነሰ ድርጊት በአለታ ወንዶ መፈጸሙን ገልጸዋል

 

ሌላው ኢትዮጵያዊ ደግሞ ለዚህ ሁሉ ድርጊት ተጠያቂው ስርአቱ ነው ሲል መንግስትን ከሷል

ከፈረንሳይ አገር ትእግስት የምትባል ሴት በሰጠችው አስተያየት ድርጊቱ ድንጋጤን እንደፈጠረባት ተናግራለች

ሌላ በውጭ አገር የሚኖር ኢትዮጵያዊ በበኩሉ የመንግስቱ ሹም የሰራው ስራ እጅግ እንዳሳዘነው ገልጾ ፣ ህዝቡ እንዲህ አይነት ግፍ ሲፈጸም ዝም ብሎ መመልከቱ ጥያቄ እንደፈጠረበት ተናግሯል

 

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የሰብአዊ መብት ተሟጋች የሆኑት ወ/ሮ ሰብለወርቅ ታደሰ ፣ ድርጊቱ ሴትነታችን፣ እናትነታችን ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያዊነታችን የተዋረደበት ጊዜ ላይ መድረሱን ያሳያል ብለዋል

ወ/ሮ ሰብለ ወርቅ ታደሰ እንዳሉት መንግስት እንዲህ አይነት ሰዎችን በዙሪያው አሰልፎ ስልጣን ለላይ ለመቆየት ማሰቡንና ፣ በስልጣን ላይ እስከቆየ ድረስ እንዲህ አይነት የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲፈጸም ችላ እንደሚል የቀደመ ልምዳቸውን በማንሳት ተናግረዋል

 

ወ/ሮ ሰብለ በመጨረሻም ህዝቡ እርምጃ መውሰድ ካልቻለ ባርነታችን መቀጠሉ አይቀሬ ነው ብለዋል

ሌላው የሰብአዊ መብቶች ተማጋች የሆኑት አቶ ብዙነጽ ጽጌ በበኩላቸው ድርጊቱ ከባህላችን የወጣ በመሆኑ ሀዘንና ድንጋጤ የተሰማቸው መሆኑን ገልጸው፣ አሁን ባለው ስርአት በህግ መፍትሄ ይመጣል ብለው እንደማያስቡ ገልጸዋል።

አቶ ብዙነህ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አጠቃላይ የስርአት ችግር የሚፈጥረው መሆኑን ተናግረዋል

 

ምንም እንኳ አሰቃቂ ድርጊቱን የፈጸመው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ቢውልም እስካሁን ድረስ ለፍርድ እንዳልቀረበ ታውቋል። ከግለሰቡ ጋር በመተባባር ወንጀል የፈጸሙ ሶስት የወረዳው ፖሊሶችም በቁጥጥር ስር አልዋሉም።

የወረዳው ባለስልጣናት በትናንትነው እለት መረጃውን ለኢሳት ያቀበለውን ሰው ለመለየት እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ተሰብስበው እንደነበር ለማወቅ ተችሎአል።