በደራሽ ጎርፍ 120ሺ ሰዎች መፈናቀላቸው ተገለጸ

ኢሳት (ግንቦት 4 ፥ 2008)

ሰሞኑን በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የጣለውን ዝናብ ተከትሎ በተከሰተው ደራሽ ጎርፍ፣ ከ120 ሺ በላይ ሰዎች እንደተፈናቀሉና፣ እስከ ግማሽ ሚሊዮን የሚደርሱት ደግሞ በዚሁ ጎርፍ ተፅዕኖ እንደደረሰባቸው፣ የኢትዮጵያ መንግስትና የሰብዓዊ ድርጅቶች ማስታወቃቸውን ሮይተርስ ገለጸ።

የአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM)ን ዋቢ አድርጎ ሮይተርስ እንደዘገበው፣ ባለፈው ወር ብቻ በስድስት ወረዳዎች በከባድ ደራሽ ጎርፍ የተፈናቀሉት ሰዎች ቁጥር 119,711 ሲሆን፣  ሌሎች የእርዳታ ድርጅቶች በመጪው ነሃሴ ላይ እስከ 15 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በጎፍሩ ተፅዕኖ ይደርስባቸዋል ማለታቸውን ትናንት ረቡዕ ዘግቧል።

በደራሽ ጎርፍ የተጠቁት ስፍራዎችም ከዚህ በፊት በምግብ እጥረት የተጎዱ አካባቢዎች መሆናቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት (UNOCHA) በቅርቡ ባሳተመው መጽሄት እንደገጸው፤ 190 ሺ ሰዎች በጎርፉ ሊፈናቀሉ ይችላሉ ማለቱን ሮይተርስ አክሎ አስነብቧል።

ድንገተኛ ጎርፍና ወንዞች በበልግ ዝናብ የተከሰቱ ሲሆን፣ በዚህም አደጋ 485,610 ሰዎች እንደተፈናቀሉና፣ የምግብ አቅርቦትንም አስተጓጉሎ እንደሚገኝ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት  (UNOCHA) ዘግቧል።

ድንገተኛ ጎርፍና የመሬት መናድ በድሬዳዋ፣ በባሌና በወላይታ ተከስቶ የሰው ህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ማስከተሉን ትናንት መዘገባችን ይታወሳል።