ሰኔ ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአሁኑ ወቅት የአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ ሰሞኑን ከመንግስት መገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ዕቅዱ የተለጠጠ መሆኑን አምነው ሙሉ በሙሉ ላለመሳካቱ ምክንያት ያሉዋቸውን ምክንያቶች ዘርዝረዋል፡፡ የመጀመሪያው የእድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በባህርይው መዋቅራዊ ለውጥን ታሳቢ ያደርጋል፡፡
ይህ ዕቅድ በራሱ ተለጥጦአል ብለዋል፡፡ የፋይናንስ ምንጭ ማፈላለጉ በራሱ ትልቅ ጫና ነበረው ያሉት ዶ/ር አርከበ የአቅም ችግር መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡ የቀጣይ የእድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተጀመሩትን በማጠናቀቅ እመርታ የምናሳይበት ነው ይላሉ፡፡
የኢህአዴግ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በዋንኛነት ከግብርና ወደኢንዱስትሪ የመዋቅር ሽግግር ለማድረግ ያለመ ቢሆንም አፈጻጸሙ ግን በራሱ በግብርናው ውስጥ የጎላ ለውጥ ሳይታይ ተጠናቆአል፡፡ በዕቅዱ ግብርናው 14 ነጥብ 9 በመቶ ለማሳደግ ያለመ ሲሆን በተጨባጭ ግን ማደግ የተቻለው በ 7 ነጥብ 15 ዓመታዊ ዕድገት መሆኑ ተነግሯል፡፡
የኢንዱስትሪ ዘርፉ እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም ለሀገራዊ ዕድገት የሚያበረክተው ድርሻ አሁንም ዝቅተኛ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ኢህአዴግ ለጥጦ ለያዛቸው ፕሮጀክቶች የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ይሆናሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የውጭ ንግድ ባለፉት ዓመታት አፈጻጸሙ መዳከሙ ሌላው ለእቅዱ አለመሳካት ምክንያት ሆኗል፡፡ በውጭ ንግድ ዘርፍ በዕቅዱ የመጀመሪያ ዓመት ማለትም በ2003 ዓ.ም ከፍተኛ ውጤት ቢገኝም ከዚያ በሃላ ባሉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት ከዘርፉ የተፈለገውን ውጤት ማግኘት ሳይቻል ቀርቶአል፡፡ የውጭ ንግዱ በተወሰኑ የግብርና ምርቶች ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ የቡና ዋጋ በዓለም ገበያ ሲወርድ አፈጻጸሙም በአንድ ጊዜ እንደሚያሽቆለቁል ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡
በአንጻሩ የገቢ ንግዱ እያደገ መምጣቱ በገቢ እና በወጩ ንግዱ መካከል ያለው ጉድለት ወደ 18 በመቶ እንዲያሻቅብ ምክንያት ሆኗል፡፡
በተጨማሪም ግዙፍ የተባሉት የባቡር፣ የስኳር፣ የማዳበሪያ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ከመጀመራቸው በስተቀር አንዳቸውም በተያዘላቸው ጊዜ ሊጠናቀቁ ያልቻሉ ሲሆን አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች በገንዘብ እጦትና በማስፈጸም አቅም ችግር ምክንያት ለመጓተትና ለብክነት መዳረጋቸው ታውቆአል፡፡
ሟቹ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በወቅቱ ያቀረቡት እቅድ የተጋነነው በሚል የሚተቹዋቸውን ሁሉ ሲያያጥሉ ነበር።አቶ አርከበ በቀድሞው ጠ/ሚኒስትር የቀረቡ እቅዶችን ሁሉ ሲያጣጥሉ መሰማታቸው ሟቹ ጠ/ሚኒስትር ቢኖሩ ኖሮ ይህን ይሉ ነበር ወይ? የሚል ጥያቄ አስነስቶባቸዋል። የአቶ አርከበ ንግግር አቶ መለስ ዜናዊን የሁሉም ነገር ፈጣሪና አድራጊ አድርገው የሚመለከታቸውን ወገኖች ሊያስከፋ እንደሚችል አስተያየቶች ይቀርባሉ።