ኢሳት (ግንቦት 19 ፥ 2008)
ዩጋንዳ መዲና ካምፓላ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሬስቶራንት (ምግብ ቤት) ላይ ከስድስት አመት በፊት በተፈፀመው የሽብር ጥቃት ሃሙስ የጥፋተኝነት ውሳኔ የተላለፈባቸው አምስት ተከሳሾች የእድሜ ልክ የእስር ፍርድ ተላለፈባቸው።
በተመሳሳይ ክስ ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ ሁለት ተከሳሾች ደግሞ የ50 አመት የእስር ቅጣት እንደ ተበየነባቸው ቢቢሲ የዩጋንዳን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔን ዋቢ በማድረግ አርብ ዘግቧል።
የሽብር ጥቃቱን በዋነኛነት አቀናብሯል የተባለው ዩጋንዳዊ ኢሳ አህመድ ሉማይ እድሜ ልክ የእስር ቅጣት ከተላለፈባቸው መካከል አንዱ ሲሆን ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች ላይ የሞት ቅጣትን ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቅ እንደነበር ታውቋል።
ይሁንና የዩጋንዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት አልፎንስ አዊኒ ዶሎ የተላለፈው ፍርድ ቅሬታን የሚፈጥር እንዳልሆነ ከውሳኔው በኋላ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
የዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ጨዋታን በመመልከት ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ ተፈጽሞ በነበረው በዚሁ ጥቃት 74 ሰዎች መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን ሶማሊያ የሚገኘው ታጣቂ ሃይል አልሻባብ ለጥቃቱ ሃላፊነትን መውሰዱም ይታወቃል።
የፍርድ ውሳኔ ከተላለፈባቸው በተጨማሪ ስድስት ተከሳሾች ከተመሰረተባቸው የሽብር ክስ ነጻ ቢሆኑም አንደኛው አነስተኛ በሆነ ክስ መከሰሱን ቢቢሲ በዘገባው አመልክቷል።
ይሁንና አምስቱ ተከሳሾች ከሽብርተኛ ክሱ ነጻ ቢባሉም ግለሰቦቹ በድጋሚ ለእስር ተዳርገው ከመዲናዋ ካምፓላ ውጭ መወሰዳቸውን የተከሳሹ ጠበቃ ለዜና አውታሩ አስረድተዋል።
ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የፖሊስ አባላት በበኩላቸው በነጻ የተሰናበቱት አምስቱ ግለሰቦች ለደህንነታቸው ሲባል ወደ አልታወቀ ስፍራ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
ተከሳሾቹ በብሪታኒያና የአሜሪካ የጸጥታ ሃይሎች ስቃይ ተፈጽሞብናል ማለታቸውን ተከትሎ የክስ ሂደቱ ተስተጓጉሎ መቆየቱ ይታወሳል።
በወቅቱ ጥቃቱን እንዲፈጸመ የገለጸው አል-ሻባብ የዩጋንዳ ወታደሮች ወደ ሶማሊያ በማሰማራት ምክንያት የበቀል ጥቃት እንደወሰደ ሲገልጽ ቆይቷል።
ለደህንነታቸው ሲባል ወደ አልታወቀ ስፍራ ተወስደዋል የተባሉት አምስቱ ተከሳሾች መቼና እንዴት እንደሚለቀቁ ግን የታወቀ ነገር የለም።