(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 16/2010)
የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ሙሉ በሙሉ ትምህርት ማቆሙ ተገለጸ።
በአዳማ ዩኒቨርስቲ ካለፈው ሀሙስ ጀምሮ ትምህርት ተቋርጧል።
በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ባለፈው ዓርብ በተነሳው ተቃውሞ የህንጻዎች መስታወት መሰባበሩንም ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቷል።
በደብረታቦር ዩኒቨርስቲ በትግራይ ልዩ ሃይልና በአማራ ልዩ ሃይል መሃል ቅዳሜ ዕለት የትኩስ ልውውጥ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
በአሶሳ ዩኒቨርስቲም ተቃውሞ ተጀምሯል።
በወልዲያ ዩኒቨርስቲ የታሰሩ ተማሪዎች ከፍተኛ ድብደባ እየተፈጸመባቸው መሆኑ ታውቋል።
ከ10ቀናት በፊት ጀምሮ በውጥረት ውስጥ የሰነበተው የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሙሉ በሙሉ ከመማር ማስተማር እንቅስቃሴ መውጣቱ ታውቋል።
የትምህርት ሚኒስቴርም ይህን ያረጋገጠ ሲሆን በዩኒቨርስቲው በተፈጠረው ረብሽ ምክንያት ትምህርት መቀጠል አልተቻለም ሲሉ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዋ ለሪፖርተር ጋዜጣ ገልጸዋል።
በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የተጀመረው ተቃውሞ መነሻው በአዲግራት ለተገደሉ የአማራና የኦሮሞ ተማሪዎች ሀዘንን ለመግለጽና ድርጊቱን ለማውገዝ እንደነበር በወቅቱ መዘገቡ ይታወሳል።
የአጋዚ ሰራዊት ግቢው ውስጥ ዘልቆ በመግባት በወሰደው ርምጃ 15 ተማሪዎች ጉዳት ደርሶባቸው በድሬዳዋ ድል ጮራ ሆስፒታል ተኝተው እንደነበርም ታውቋል።
ከዚያን ጊዜ ወዲህ በዩኒቨርስቲው መረጋጋት እንደሌለ የገለጹት የኢሳት ምንጮች በመጨረሻም ተማሪዎች ግቢውን ለቀው በመውጣታቸው ዩኒቨርስቲው ሊዘጋ መቻሉን ተናግረዋል።
በአዳማ ዩኒቨርስቲም በተመሳሳይ የትምህርት ሂደቱ መቋረጡን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በቅርቡ የፋሲል ከነማ የእግርኳስ ቡድን ከአዳማ አቻው ጋር ለመጋጠም ወደ አዳማ በመጣ ጊዜ የዩኒቨርስቲው የአማራና የኦሮሞ ተማሪዎች ያዋቀሩት ኮሚቴ ደማቅ አቀባበል ማደረጉን ተከትሎ የመንግስት የደህንነት ሃይሎች በተማሪዎች ላይ ድብደባ መፈጸማቸውን የኢሳት ምንጮች ጠቅሰዋል።
ላለፉት 15 ቀናትም የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች በአፈና ውስጥ መቆየታቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ኢሳት ያነጋገረው አንድ ተማሪ እንደገለጸው የአዳማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እስረኛ ሆነዋል።
ከመኝታ ክፍል ውጪ የተገኘ ተማሪ ይደበደባል። በርካታ ተማሪዎች ተጎድተው በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ባለፈው ዓርም ምሽት በተጀመረው ተቃውሞ የዩኒቨርስቲው አንዳንድ ህንጻዎች መስታወቶች በድንጋይ መሰባበራቸውን ለማወቅ ተችሏል።
የዩኒቨርስቲው የምህንድስና ትምህርት ክፍል ቤተመጽሃፍት ህንፃ መስታወት በከፊል ተሰብራል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ወደዩኒቨርስቲው በመግባት በተማሪዎች ላይ ድብደባ መፈጸሙ ታውቋል።
በአሶሳ ዩኒቨርስቲ ባለፈው ዓርብ በተካሄደው ተቃውሞ የህወሃት መንግስት ከስልጣን እንዲወርድ ተጠይቋል።
ከትላንት በስትያ ቅዳሜ በደብረታቦር ዩኒቨርስቲ ቅጥር ግቢ አካባቢ ከፍተኛ የተኩስ እሩምታ እንደነበር የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በዩኒቨርስቲው የትግራይ ተማሪዎችን ለመውሰድ ከትግራይ በመጡ ልዩ ሃይል አባላትና የታጠቁ ደህንነቶችና በአማራ ልዩ ሃይል መካከል የተደረገው የተኩስ ልውውጥ ያደረሰው ጉዳት ባይኖርም ለአንድ ሰዓት ገደማ የዘለቀ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
የአማራ ልዩ ሃይል ያለዩኒቨርስቲው ፍቃድ መውሰድ አትችሉም በሚል የትግራይ ልዩ ሃይል አባላትን በመከልከላቸው የተነሳ የተኩስ ልውውጡ መደረጉም ተጠቅሷል።
በሌላ በኩል ከወልዲያ ዩኒቨርስቲ ተወስደው በእስር ቤት የሚገኙ ተማሪዎች ከፍተኛ ድብደባ እየተፈጸመባቸው መሆኑን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ከአንድ ሳምንት በፊት በዩኒቨርስቲው በተነሳ ተቃውሞ ህንጻ መቃጠሉን ተከትሎ በርካታ ተማሪዎች የታሰሩ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሰባት ሴቶችና 10 ወንዶች ዛሬ መፈታታቸው ታውቋል።
ሌሎቹ ያሉበት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ወደ ትግራይ ተወስደው በእስር ላይ የሚገኙም እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል።