ሚያዚያ ፳፮(ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በዱባይ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላት ለገልፍ ኒውስ እንደገለጹት ፣ በቤት ሰራተኛነት ለመቀጠር ከ500 ያላነሱ ኢትዮጵያውያን በየቀኑ የተለያዩ አየር መንገዶችን በመጠቀም በህገወጥ መንገድ ይገባሉ።
በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አገራችን ገብተዋል የተባሉ ሰላሳ ኢትዮጵያዊያን ከዱባይ ወደ አገራቸው መላካቸውን የኤምሬትስ የስደተኞች ጉዳይ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በኤምሬትስ፣ኩዌትና በሳኡዲ አረቢያ በሕጋዊ መንገድ ከገቡ በኋላ የተሰጣቸው ቪዛ ሲጠናቀቅ በሕገወጥነት ነዋሪነት እንደሚቀሩ ዘገባው አመልክቷል።
በተጨማሪም በግብጽ በሕገወጥ መንገድ በሜድትራኒያን ባሕር ላይ በጀልባ ለመጓዝ ወደ አውሮፓ ለመግባት ሲሞክሩ የነበሩ 159 ኢትዮጵያዊያን፣ ኤርትራዊያን፣ ሶማሊያዊያን፣ ሱዳናዊያንና የኮሞሮስ ዜጎችን መያዙን የአገሪቱ የድንበር ፓሊስ አስታውቋል። ስደተኞቹ ከሰሜናዊ ምስራቅ አሌክሳንደሪያ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አቡ ቂር የባህር ዳርቻ እሁድ ምሽት ላይ መያዛቸውንና በተለይ ሶስቱ የጀልባዋ አሽከርካሪዎች ላይ ምርመራ መቀጠሉንና ስደተኞቹ የሕክምና እርዳት እየተደረገላቸው መሆኑን የፓሊስ ቃል አቀባዩን ጠቅሶ ሚና የዜና አውታር ዘግቧል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከሊቢያ ወደ አውሮፓ ሕገወጥ ስደተኞችን ሲያዘዋውር የነበረው ኢትዮጵያዊው የ58 ዓመቱ ጎልማሳ ሃዱሽ አባዩ ኪዳኑ የዘጠኝ ዓመት እስራት ተፈረደበት። ግለሰቡ ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት ወደ ማልታ ደሴት የገባ ሲሆን ሕገወጥ ፓስፓርት በመጠቀም ስዊዘርላንድ መሄዱንና የስዊዝ መንግስት ይዞ ወደ ማልታ ተላልፎ መሰጠቱን ማልታ ኢንዲፔንደንት ጋዜጣ ዘግቧል።