ሚያዝያ ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ረዩተርስ ከካይሮ እንደዘገበው በሳውድ አረቢያ የሚመራው የጥምር ሃይል በየመን በአንድ አለማቀፍ የበጎ አድራጎት ጽህፈት ቤት ላይ በወሰደው ጥቃት 5 ኢትዮጵያውያን ሲገደሉ 10
የሚሆኑት ደግሞ ቆስለዋል።
ጥቃቱ የሃውቲ ሚሊሺያዎች ዋና ደጋፊ ተደርጎ በሚቆጠረው ሃጅያ ግዛት ውስጥ በሚገኘው ማይዲ ከተማ ላይ በከባድ መሳሪያና በአየር መፈጸሙን የዜና ድርጅቱ ገልጿል። የሳውድ አረቢያ ጦር ከሃውቲ ሚሊሺያዎች ጋር መዋጋቱን ተከትሎ፣
ሚሊሺያዎቹ የሳውድ አረቢያን ድንበር ጥሰው መግባታቸውን ማስሪያ የቴሌቪዥን ጣቢያ ማሳየቱን ረዩተርስ ዘግቧል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ ባንኪሙን ከስልጣን በተባረሩት ፕሬዚዳንት ሃዲ እና በሚሊሺያዎቹ መካከል ንግግር ለማስጀመር ከሳምንት በሁዋላ በጄኔቭ ቀጠሮ ይዘዋል።
የኢትዮጵያውያኑን መገደል በተመለከተ የመን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲም ሆነ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ምንም መግለጫ አልሰጡም።