በየመን የታገቱ ከ3 ሺ በላይ ሴቶች በተደጋጋሚ ጊዜ ተደፈሩ

መጋቢት 6 ቀን 2004 ዓ/ ም

ኢሳት ዜና:-በሃርደሀ የመን የታገቱት ከ3 ሺ በላይ ሴቶች በተደጋጋሚ ጊዜ እንደተደፈሩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽነር አስታወቀ

ኢትዮጵያውያኑ ሀርዳህ ከተማ ውስጥ ሻርቂያ በምትባል መንደር ለረጅም ጊዜ ታግተው ቆይተዋል።  በርካቶቹ የውስጥ ሱሪ ብቻ ለብሰው መገኘታቸውን ኮሚሽኑ ገልጧል። ድርጊቱን ያጋለጡት ሁለት ሰዎች በአጥር ዘልለው ለማምለጥ በመቻላቸው ነው።

ሀርዳህ ውስጥ የወንጀልምርመራ ሰራተኛ የሆኑት አሊ አብራሂም ” ለ15 አመታት በምርመራ ስራ ላይ ሲቆዩ፣ እንዲህ አይነት ነገር ተፈጽሞ አለማየታቸውንና በኢትዮጵያውያኑ ላይ የደረሰው ግፍ ለመግለጥ አይቻልም።” ብለዋል፡

ሌላ ባለስልጣን ለተባባሩት መንግስታት ድርጅት የዜና ወኪል እንደገለጡት ” ምን ያክል ሰዎች እንደተገደሉ አናውቅም፣ ግን ይህ የተለየ ነገር ነው። ለዚህን ያክል ጊዜ ሰዎች ታግተው መቆየታቸው የሚገርም ነው”ብለዋል።

ስደተኞቹ ቤተሰቦቻቸው የማስለቀቂያ ገንዘብ እስከሚከፍሉ ድረስ ይደበደቡና የተለያዩ አሰቃቂ ድርጊቶች ይፈጸምባቸው እንደነበር በየመን የተመድ የዩኔን ኤች ሲ አር ተወካይ የሆኑት አቶ ብርሀነ ተክሉ ነጋ ተናግረዋል።

አቶ ተክሉ አክለው ሲናገሩ ባለፈው አመት ውስጥ ከታገቱ 3ሺ ሴቶች ማካከል አብዛኞቹ በተደጋጋሚ ተደፍረዋል። አንዲት ወጣት አባቱዋ 5 ሺ ዶላር ከላኩ በሁዋላ መፈታቱዋን፣ ተገዳ በመደፈሩዋም መጸነሱዋን ይሁን እንጅ ልጁን ለመውለድ ፈቃደኛ አለመሆኑንና ለማስወረድ እንደምትፈልግ ተናግራለች።

የታገቱት ኢትዮጵያውያኑ የሴቶችን መደፈር ለመካለከል ሲሞክሩ ራሳቸውም እንደሚደፈሩ አንድ በግዳጅ የተደፈረ ጉዳተኛ ለኢሪን ተናግሯል።

ለ50 ቀናት የተደበደበ የ30 አመት ወጣት አንድ አይኑ መጥፋቱን ፣ በድብደባ የቆሳሰለውን መላ አካሉን ለኢሪን ጋዜጠኛ አሳይቷል። ምንም እንኳ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰው ግፍ የሰው ልጅ አእምሮ ሊሸከመው ከሚችለው በላይ እየሆነ ቢመጣው፣ በቅርቡ በተደረገ ጥናት አገራቸውን ለቀው ወደ የመን የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያኑ ቁጥር በ100 እጅ ጨምሯል። በ2011 ብቻ 65 ሺ ኢትዮጵያውያን የመን ገብተዋል።

ባለፈው የካቲት ወር ፖሊስ 128 ኢትዮጵያንንን ያገቱ 2 የመናዊያንን ማሰሩ ይታወቃል።

የህወሀቱ መስራች የሆኑት አቶ ስብሀት ነጋ ሰሞኑን በአገር ውስጥ በሚታተም አንድ ጋዜጣ ላይ  የአሁኑዋን ኢትዮጵያ ከአጼ ሀይለስላሴ ዘመን ከነበረችው ኢትዮጵያ ጋር አነጻጽረው ሲጽፉ  የዛሬዋ ኢትዮጵያ የሰው ልጅ የማይሰደድባት አገር ሆናለች ብለዋል። የህወሀቱ ባለስልጣን ንግግር በስደት በሰሀራ በረሀና በየመን ባህረ ሰላጤ ላለቁት ኢትዮጵያውያን እንዲሁም በአረብ እስር ቤቶች ታጉረው ለሚገኙ በብዙ ሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ታላቅ ስድብ ሆኖ ተቆጥሯል።

ኢትዮጵያ በአንድ በኩል የ11 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት የሚለፈፍባት ፣ በሌላ በኩል ግን በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በየቀኑ ነፍሳቸውን ለማዳን የሚሰደዱባት አገር ሆናለች። 

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide