በየመን የሚገኙ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለከፋ የሰብዓዊ ቀውስ ተጋልጠዋል ተባለ

ኢሳት (ህዳር 8 ፥ 2009)

በየመን በስደት ላይ የሚገኙ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለከፋ የሰብዓዊ ቀውስና በሃገሪቱ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ተጋላጭ መሆናቸው ስጋት እንዳሳደረበት የአለም አቀፍ የሰደተኞች ድርጅት (IOM) አስታወቀ።

ሰሞኑን በሳውዲ አረቢያ የሚመራው ጥምር ሃይል ለተወሰነ ጊዜ የሚፈጸመውን የአየር ጥቃት ማቆሙን ተከትሎ ድርጅቱ መውጫን አጥተው የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ከሃገሪቱ ለማስወጣት ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

ይሁንና የስደተኞቹ ቁጥር ከፍተኛ መሆኑንና ያሉበት የጤና ሁኔታ ኢትዮጵያውያኑ ወደሃገራቸው ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል ሲሉ በየመን የስደተኛ ተቋሙ የአስቸኳይ ጊዜ ሃላፊ የሆኑት ሞሃመድ አብዲከር ይፋ አድርገዋል።

“በየመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ደህንነት እጅጉኑ አስደንጋጭና አሳዛኝ ነው ሲሉ የገለጹት ሃላፊው በመቶዎች የሚቆጠሩ እነዚሁ ስደተኞች ለአየር ጥቃት እና በየመን እየተካሄደ ባለው ግጭት ተጋላጭ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ኢትዮጵያውያኑን ወደ ጅቡቲ በማጓጓዝ ወደ ሃገራቸው የሚመለሱበት ሁኔታ እንዲመቻች ከተለያዩ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ አክሎ ገልጿል።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ከ600 በላይ ስደተኞች ወደ ጅቡቲ እንዲገቡ የተደረገ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያኑ ወደ ሃገራቸው ለመጓጓዝ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የሰደተኞቹ ሃላፊዎች አስታውቀዋል።

ሴቶችና ህጻናት ወደ ጅቡቲ እንዲጓጓዙ ከተደረጉት ስደተኞች መካከል እንደሚገኙበት ታውቋል።

ይሁንና የአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጁት (IOM) ኢትዮጵያውያኑ በህጋዊ መንገድ ከየመን ለማስወጣት ጥረትን እያደረገ ቢገኝም የየመን ባለስልጣናት ያለምንም ታዛቢነት ኢትዮጵያውያኑን በተናጥል ወደ ጅቡቲ እንዲሰፍሩ እያደረገ ያለው እርምጃ ስጋት መፍጠሩን ሃላፊዎች ይፋ አድርገዋል።

በቅርቡ ወደ ጅቡቲ በጀልባ ተወስደው ያለመጠለያና ምግብ እንዲሰፍሩ ከተደረጉ ኢትዮጵያውያን መካከል በትንሹ 24 የሚሆኑት ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ የሰደተኛ ድርጅቱ ከ200 የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ጦርነት እልባት ካላገኘባት የመን ማስወጣት የቻለ ሲሆን፣ የሃገሪቱ ባለስልጣናት ያለማንም ታዛቢ እየተጓጓዙ ያለው ኢትዮጵያውያን ቁጥር ሊታወቅ አለመቻሉን ከድርጅቱ ከተገኘው መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

ይሁንና የጅቡቲ ባለስልጣናት በአሳዛኝ ሁኔታ በግዳጅ እንዲሰፍሩ ከተደረጉት ስደተኞች መካከል በትንሹ 24ቱ መሞታቸውን ማረጋገጫ እንዲሰጡ IOM በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

የኢትዮጵያውያኑ ሞትና ሁኔታ በተመለከተ ከመንግስት በኩል የተሰጠ ምላሽ የሌለ ሲሆን፣ የሰደተኛ ኮሚሽኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በየመን የሚገኙ ስደተኞችን ለመታደግ እየተደረገ ያለውን ጥረት እንዲያግዙ ጥሪውን አቅርቧል።

ባለፈው አንድ አመት ብቻ ከ70ሺ የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን በእርስ በርስ ጦርነት በምታተመሰው የመን መሰደዳቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ጦርነት እየተካሄደ ባለበት ወቅትም የኢትዮጵያውያኑ ስደት አለመቋረጥ ስጋት ማሳደሩን የስደተኛ ድርጅቶች ሲገልጹ ቆይተዋል።