በየመን እርስ በእርስ ጦርነት መውጫ አጥተው የነበሩ 485 ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራቸው ሊመለሱ ነው

ኢሳት (መጋቢት 20 ፥ 2008)

የአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) በየመን ካለው ጦርነት መውጫን አጥተው የነበሩ 485 ስደተኛ ኢትዮጵያውያንንን መታደጉን ማክሰኞ ገለጠ።

ከኢትዮጵያ ጦርነት እልባት ወደ አላገኘባት የመን የሚደረገው ስደት መባባስ ስጋት እንደፈጠረበት ያስታወቀው ድርጅቱ ለአደጋ ተጋልጠው መውጣት ከቻሉት መካከል 122ቱ ሴቶች እንዲሁም 101 ወጣቶችና አንድ ህጻን እንደሚገኙበት አመልክቷል።

እነዚሁ ስተደኛ ኢትዮጵያውያን በጎረቤት ጅቡቲ በኩል አድርጎ በአውቶቡስ ወደ ኢትዮጵያ ለማጓጓዝ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አፍሪካን ፕሬስ ኤጀንሲ ድርጅቱን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

ከጦርነት ማውጣት የቻሉት ኢትዮጵያውያን ለታጣቂዎች ክፍያን በመፈጸም አልያም በራሳቸው ማምለጥ የቻሉ እንደሆነ የገለጸው ድርጅቱ ኢትዮጵያውያኑን ወደሃገራቸው ለመመለስ በየመን የሚገኘው ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረጉን አውስቷል።

በፈረንጆቹ አመት 2015 አም ወደ 80ሺ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ወደየመን የተሰደዱ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ስደተኞች በጦርነቱ ምክንያት ከሃገሪቱ መውጣት ሳይችሉ መቅረታቸው ይነገራል።

የአለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅትም እነዚህኑ ኢትዮጵያውያን ለመታደግ የጸጥታና የበጀት እጥረት ገጥሞት እንደሚገኝም አስታውቋል።

ይሁንና ኢትዮጵያውያኑ ከየመን መውጫን አጥተው ባሉበት ሁኔታ አሁንም ድረስ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደየመን በመሰደድ ላይ መሆናቸውን ተጨማሪ ስጋትን ፈጥሮ እንደሚገኝ የስደተኞቹ ድርጅት አክሎ ገልጿል።

በየመን ያለው አለመረጋጋት በስደተኛ ኢትዮጵያውያኑ ላይ የደረሰን ጉዳት በአግባቡ ለማወቅ እንዳላቻለም ተነግሯል።