ኢሳት (ኅዳር 27 ፥ 2009)
በየመን እየተካሄደ ካለው የእርስ በርስ ጦርነት መውጫን አጥተው የሚገኙ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ደህንነታቸው አደጋ ውስጥ መውደቁን የአለም አቀፍ የሰደተኞች ድርጅት (IOM) ማክሰኞች አስታወቀ።
ድርጅቱ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ለመታደግ የህይወት አድን ዘመቻ በቅርቡ ቢጀምርም በሃገሪቱ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ከየመን ለመውጣት የሚፈልጉ ስደተኞችን ማውጣት እንዳልቻለ ገልጸዋል።
ይሁንና ባለፈው ወር ብቻ የስደተኞቹ ተቋም 150 ኢትዮጵያውያንን ከየመን ማስወጣት የቻለ ሲሆን ሰንዓ ከተማን ተቆጣጥሮ የሚገኘው የሃገሪቱ መንግስት በተናጠል ዕርምጃ በርካታ ስደተኞችን በሃይል ወደ ጅቡቲ እየመለሰ መሆኑ ታውቋል።
በየመን ያሉ መገኛኛ ብዙሃን የአለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት ስደተኞቹን በሃይል ለማስወጣት በሚደረገው ዘመቻ ላይ ተሳታፊ ነው ሲሉ ሰሞኑን ዘገባ አቅርበዋል።
ይሁንና ማክሰኞች በጉዳዩ ላይ ምላሽን የሰጠው ድርጅቱ ኢትዮጵያውያኑ በሃይል ለመመለስ በተደረገ ሂደት ላይ ተሳታፊ አለመሆኑን ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
የአለአም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት መርህ ተመላሽ ስደተኞችን በሃይል መመለስ ይከለክላል ያለው ተቋም ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ የተደረጉ ስደተኞች በገዛ ፈቃዳቸው ብቻ መመለሳቸውን ገልጿል።
ባለፈው አንድ አመት 10ሺ ኢትዮጵያውያን በድርጅቱ ድጋፍ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ መደረጉ ታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን በተያዘው የፈረንጆች አመት ብቻ ወደ 90ሺ አካባቢ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጦርነት ዕልባት ወዳላገኘባት የመን መሰደዳቸውን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
የስደተኞቹ ፍልሰት ስጋት እንዳሳደረባት የሚገልጸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለፈው አመት በተመሳሳይ መልኩ ወደ 80ሺ ኢትዮጵያውያን ወደ የመን መሰደዳቸውን አመልክቷል።
ይሁንና በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከጦርነት ለመውጣት ሙከራን ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው መቅረቱትንና ህይወታቸው አደጋ ውስጥ መሆኑን የስደተኞቹ ተቋም ይገልጻል።
በእስካሁኑ ዘመቻ ከየመን መውጣት የቻሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከፍላጎቱ አንጻር ሲታይ እዚህ ግባ የማይባል ነው ሲሉ ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
ባለፈው ወር በሃይል ወደ ጎረቤት ጅቡቲ እንዲሰፍሩ ከተደረጉ ከ70 በላይ ስደተኞች መካከል ከ20 የሚበልጡት በደረሰባቸው እንግልት ምክንያት ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።
በጉዳዩ ዙሪያ የኢትዮጵያም ሆነ የጅቡቲ ባለስልጣናት እስካሁን ድረስ የሰጡት ምላሽ የለም።