በዞን 9 ጸሃፊዎች ላይ ማስረጃ ሊቀርብ አልቻለም ተባለ

ሚያዝያ፩(አንድ ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ብሉምበርግ ዞን 9 በመባል በሚጠሩት ወጣት ጸሃፊዎችና ጋዜጠኞች ላይ የመንግስት አቃቢ ህግ ጠንካራ ማስረጃ ለማቅረብ አለመቻሉን ጠበቃውን አቶ አምሃ መኮንንን በመጥቀስ ዘግቧል።

በሽብርተኝነት ወንጀል የተከሰሱት 6 የዞን ዘጠኝ እና 3  ጋዜጠኞች ላለፉት 10 ወራት በእስር ላይ ከቆዩ በሁዋላ፣ ፍርድ ቤቱ በቅርቡ ምስክሮችን የመስማት ሂደቱን ጀምሯል።  ይሁን እንጅ እስካሁን ባለው ሂደት የቀረቡት ምስክሮች ጸሃፊዎችና ጋዜጠኞች ተይዘው ቤታቸውና መስሪያ ቤታቸው ሲፈተሽ በታዛቢነት የነበሩ እንጅ ፣ ተከሳሾቹ በተለይም ክስ ከቀረበባቸው ከግንቦት7 እና ከኦነግ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የሚያመላክት ምስክር ሊቀርብባቸው አልቻለም።

አቃቢ ህግ 35  የሰው ምስክሮች አሉኝ ብሎ ለፍርድ ቤቱ ቢያስታውቅም ” ምስክሮችን አላገኘሁዋቸውም” በሚል ሰበብ እስካሁን ሊያቀርባቸው አልቻለም። አቃቢ ህግ ወንጀሉን ያስረዱልኛል የሚላቸውን የሰው ምስክሮች በመጪው ወር መጨረሻ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤት ትእዛዝ አስተላልፏል።

በኢትዮጵያ ባለው የተበለሸ  የፍትህ ስርአት ዜጎች ዋስትና አጥተው በእስር እየተሰቃዩ ነው በማለት አለማቀፍ ድርጅቶች በተደጋጋሚ ክስ ያሰማሉ። እውቁ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ በርካታ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲካኞችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በሽብር ወንጀል ተወንጅለው በእስር ቤት ይሰቃያሉ። መንግስት ከአለማቀፉ ማህበረሰብ እስረኞችን እንዲፈታ ተደጋጋሚ ጥሪ ቢቀርብለትም ፣ ለመፍታት ፈቃደኛ አልሆነም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በማእከላዊ እስር ቤት የሚገኙ በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ እስረኞችን ፣ መንግስት የይቅርታ ደብዳቤ እንዲፅፉ ለማግባባት እየሞከረ መሆኑን የደረሰን መረጃ ያመለክታል። መንግስት የይቅርታ ደብዳቤ ከጻፉ እንደሚፈታቸው ቢገልጽም፣ የውስጥ ምንጮች እንደሚሉት ግን ፣ በአብዛኛው ተከሳሾች ላይ በቂ ማስረጃ በመጥፋቱ መንግስት እስረኞቹ የሚጽፉትን ደብዳቤ እንደማስረጃ በመጠቀም በፍርድ ቤት ሊወነጅላቸው ያስባል። ከአዲስ አበባ እና ከተለያዩ ክልሎች የመጡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን በማእከላዊ እስር ቤት በስቃይ ላይ ይገኛሉ።