የካቲት ፲፫ ( አሥራ ሦስት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአብዛኛው የቀድሞ የህወሃት የጦር መኮንኖችና አባላት በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከልማት ባንክና ከንግድ ባንክ እንዲበደሩ በማድረግ በጋምቤላ ሰፋፊ መሬቶችን እንዲገዙ ሁኔታዎችን ማመቻቸታቸው የሚነገርላቸው የልማት ባንክ የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ባህረን ጨምሮ ሌሎች የልማት ባንክ እና የንግድ ባንክ የስራ ሃላፊዎች ከአገር መውጣታቸው የታወቀ ሲሆን፣ ድርጊቱ ግለሰቦቹንና ከእነሱ ጀርባ ያሉትን ባለስልጣናት ሆን ብሎ ከወንጀል ለመከላከል የተደረገ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል።
የግብርና ኢንቨስትመንት ሀገራዊ ንቅናቄ በሚል ታህሳስ 15 ቀን 2009 በግዮን ሆቴል የተካሄደው ጥናታዊ ኮንፈረንስ፣ እንደ ጋምቤላ ባሉ ክልሎች በግብርና ኢንቨስትመንት ስም ከፍተኛ ዝርፊያ መፈጸሙ ይፋ አድርጎ ነበር።
ከግብርና ኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ ከልማት ባንክ እና ከንግድ ባንክ በድምሩ 4 ነጥብ 27 ቢሊየን ብር ብድር 200 ያህል ባለሃብቶች የወሰዱ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ገንዘቡን ጥቅም ላይ ማዋል የቻሉት 18 በመቶ ብቻ መሆናቸው በጥናት የተረጋገጠ ቢሆንም፣ በዚህ ዝርፊያ ውስጥ እጃቸው ያለበት የባንኮቹ ከፍተኛ ሃላፊዎችና ባለሃብቶቹ እስካሁን ክስ አልተመሰረተባቸውም።
በጋምቤላ ክልል መሬት የተረከቡ 623 ባለሃብቶች 630 ሺ 518 ሄክታር መሬት ለማልማት የወሰዱ ሲሆን በአሁኑ ወቅት መልማት የሚጠበቅበት 405 ሺ 572 ሄክታር መሬት ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ ግን በተጨባጭ ጥቅም ላይ የዋለው 15 በመቶ ያህሉ መሬት ብቻ ነው፡፡
ከ200 ባለሃብቶች ውስጥ 12 ያህሉ ከንግድ ባንክ፣ 188 ደግሞ ከልማት ባንክ ተበድረዋል፡፡ለእነዚህ ባለሃብቶች በድምሩ 4 ነጥብ 27 ቢሊየን ብር ተከፋፍሏል። ምንም እንኳ ከጋምቤላ መሬት ጋር በተያያዘ እስካሁን ክስ ባይመሰረትም፣ በቤንሻንጉል ክልል ለተፈጸመው ከፍተኛ የመሬት ዝርፊያ ክስ ለመመስረት እንቅስቃሴ መጀመሩን ኢሳት ከሳምንት በፊት ዘግቦ ነበር።
ክሱ በዋናነት “ሰባቱ ኮከቦች” ተብለው በሚጠሩት በአቶ ሳለ እግዚአብሄር በርሄ፣ አቶ ኃይሉ ነጋ፣ ሻለቃ አዕምሮ ገ/ክርስቶስ፣ ሻለቃ ኪዱ ጣዕም፣ ኮማንደር ሙሉ ሁሉፍ፣ ኮማንደር ትርሃስ ገ/ዮሐንስ እና ጄኔራል ዮሐንስ አለም ሰገድ ላይ ያነጣጠረ ሲሆን፣ ግለሰቦቹ 113 ሚሊዮን ብር ከባንክ ወስደው የተረከቡትን መሬት ከማልማት ይልቅ በአዲስ አበባ የመሬት ሽያጭ መሳተፋቸው ለጠ/ሚኒስትር ቢሮ መረጃው እንደደረሰ ምርመራ እንዲጀመር ለጸረ ሙስና ኮሚሽን ትእዛዝ ተላልፏል።
ይሁን እንጅ ግለሰቦቹ አስቀድመው ከአገር የወጡ በመሆኑ፣ ክሱ በምን መልኩ እንደሚቀጥል ማረጋገጥ አልተቻለም።
በዚሁ ክስ የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት የነበሩትን አቶ ኢሳያስ ባህረ፣ም/ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ እና የብድር አገልግሎት፣ አቶ ገነነ ሩጋ፣ ም/ ፕሬዝዳንት እና የኮርፖሬት አገልግሎት፣ እንዲሁም አቶ ግርማ ወርቄ ም/ ፕሬዝዳንት ና የድጋፍ ሰጪ አገልግሎት ኃላፊዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያስችል መረጃ በመሰብሰብ ላይ መሆኑን ዘግበን የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ለኢሳት የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ግን ስማቸው የተጠቀሰው አብዛኞቹ ባለስልጣኖች አስቀድመው ከአገር እንዲወጡ ተደርጓል።
በጋምቤላና እና በቤንሻንጉል የተፈጸመውን የመሬት ዝርፊያ በተመለከተ ሁለት ቡድኖች መፈጠራቸውን ምንጮች ይገልጻሉ። አንደኛው ክፍል ግለሰቦቹ ብቻ ሳይሆኑ ከእነሱ ጀርባ ያሉትም ተጣርቶ ክስ ይመስረትባቸው ሲል፣ ሌላው ቡድን ደግሞ ክሱ አንዱን ቡድን ለማጥቃት ሆን ተብሎ የሚቀነባበር ነው ይላል። በጌታቸው አሰፋ በሚመራው የደህንነት መዋቅርና ለዚህ መዋቅር እውቅና በማይሰጠው በጄ/ል ሳሞራ የኑስ በሚመራው የመከላከያ ሰራዊት ደህንነት መካከል የሚታየው አለመግባባት እየጨመረ መሆኑ ይነገራል። አብዛኞቹ በሙስናው ተዘፍቀው የሚገኙት የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ ባለስልጣናት የነበሩ መሆናቸው፣ የደህንነት መስሪያ ቤቱ ጄ/ል ሳሞራን ለማጥቃት እንደመልካም አጋጣሚ እየተጠቀመበት መሆኑን ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች አስተያየታቸውን ይገልጻሉ።
ከፍተኛ ሃብት የዘረፉት ባለስልጣኖች ከህወሃት ከፍተኛ ባለስልጣናት ከለላ ካልተሰጣቸው በስተቀር በቀላሉ ከአገር ሊወጡ እንደማይችሉ እነዚህ ወገኖች ይገልጻሉ። ከሁሉም በላይ ብድር እንዲወስዱ ሲወሰን የነበሩ ቃለጉበኤዎች ሆን ተብሎ ከባንኩ ማህደር እንዲጠፉ መደረጉ የጉዳዩን ውስብስብነት የሚያሳይ ነው። ሰነዶች መጥፋታቸውን ተከትሎ በወቅቱ የባንኩ የቦርድ ሰብሰባቢ የነበሩት በእስር ላይ የሚገኙት አቶ መላኩ ፋንታ ብድሩ እንዴት እንደተሰጠ የሚያውቁትን እንዲናገሩ በተጠየቁበት ወቅት፣ ለመናገር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።