በዝምባብዌ እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ራሳቸውን ስተው ሆስፒታል ገቡ

የካቲት ፲ ( አሥር )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሕገወጥ መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ሲሞክሩ ዝምባብዌ ውስጥ ተይዘው የታሰሩ 54 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በርሃብ እና ድካም ተጎሳቁለው ራሳቸውን በመሳት ወድቀዋል።
ከኢትዮጵያኑ ስደተኞች ውስጥ ስምንቱ በከፍተኛ ሕመም ራሳቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው ሆስፒታል ገብተዋል። ማንነታቸውን የሚገልጽ ምንም ዓይነት ሕጋዊ የጉዞ ሰነዶች ሳይዙ በምእራባዊ ዝምባብዌ ኒኮልሰን ክፍለሃገር በጊዋንዳ ግዛት ሲያቆራርጡ ባለፈው ዓርብ በጸጥታ ሃይሎች መያዛቸውን እና በአገሪቱ የስደተኞች ሕግ ተከሰው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተደርገዋል።
የጊዋንዳ ሆስፒታል ሜዲካል ዶክተር የሆኑት ዶ/ር ፑርጊ ቺምብሪግዋ እንዳሉት ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች በከፍተኛ የውሃ ጥም የምግብ እጥረት ምክንያት አካላቸው መጎዳቱን እና በከፍተኛ ድርቀት መጠቃታቸውን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞቹ እድሜያቸው ከ17 እስከ 27ዓመት የሚገመት ሲሆን፣ ከሕክምና ማእከሉ ወደ ተጨናነቀው እስር ቤት ተወስደዋል። የጊዋንዳ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ኦቢዲየንስ ማታሬ ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች የተያዙበት ሁኔታ አግባብ አይደለም ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። ቢትብሪጅ በሚገኘው የስደተኞች ማቆያ እስር ቤት ውስጥ በጣም በተጨናነቀ ጠባብ እስር ቤት መታገታቸውንም መስክረዋል።
ከኢትዮጵያኑ ጋር አብሮ የተያዘው የመኪናው አሽከርካሪ ኖርማን ዱቤ ሕጋዊ መረጃ ያልያዙ ስደተኞችን በመጫን ወደ ዝምባብዌ እንዲገቡ በማድረግ ወንጀል ተከሶ ፍርድ ቤት ቀርቦ የ500 ዶላር መቀጮ እና የሁለት ወራት እስራት ተበይኖበታል።
ባለፈው ዓመትም ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ተይዘው ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት በርሃብ መጎዳታቸውን በመግለጽ ፍርድ ቤት ውስጥ ማልቀሳቸውን ዚም ኒውስ ኔት አክሎ ዘግቧል።