በዛምቢያ የ19 ኢትዮጵያውያን ህይወት አለፈ

ኢሳት (ሰኔ 9 ፥ 2008)

የዛምቢያ መንግስት በዕቃ መጫኛ ተሽከርካሪ (ኮንቴይነት) ከሃገሪቱ ወደ ጎረቤት ኮንጎ በማቅናት ከነበሩ 73 ስደተኛ ኢትዮጵያውያን መካከል 19 ህይወታቸው ማለፉን አርብ አስታወቀ።

የዛምቢያ ሰሌዳ ቁጥርን በለጠፉ ተሽከርካሪ ይጓዙ የነበሩት ኢትዮጵያውያን በድንበር አካባቢ ከፍተኛ የጩኸት ድምፅ በማሰማታቸው የኮንጎ የድንበር ተቆጣጣሪዎች ተሽከርካሪውን አስቁመው አደጋው ሊረጋገጥ መቻሉን የዛምቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

የዕቃ መጫኛ ተሽከርካሪው አሳና ጥራጥሬዎችን ጭኖ በመጓዝ ላይ የነበረ ሲሆን፣ የኮንጎ የጸጥታ ሃይሎች በተሽከርካሪው ላይ ፍተሻን ባካሄዱ ጊዜ ኢትዮጵያውያን ስደተኞቹ በተጨናነቀ ሁኔታ ተደብቀው መገኘታቸውን ሉሳካ ታይምስ ጋዜጣ የዛምቢያ መንግስት መግለጫ ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

አለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅትና የዛምቢያ መንግስት ከአደጋው የተረፉ ኢትዮጵያውያንን ወደ መዲናይቱ ሉሳካ ለማጓጓዝ እና አስፈላጊውን የመጠለያና የምግብ እንዲሁም የህክምና አገልግሎት ለማቅረብ ጥረት እያደረጉ መሆኑ ታውቋል።

ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ወደ ሃገሪቱ መቼና በምን ሁኔታ እንደገቡ ምርመራ የተጀመረ ሲሆን፣ አደጋ ያጋጠማቸው ኢትዮጵያውያን ከጎረቤት ታንዛኒያ ሳይገቡ አልቀረም የሚል ጥርጣሬ መኖሩን የዛምቢያ ፖሊስ ገልጿል።

የዛምቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት ናማቲ ሺንካ ኢትዮጵያውያን ስደተኞቹን ሲያጓጉዙ የነበሩት የሃገሪቱ ዜጎች ለህግ ቀርበው አስፈላጊውን ፍትህ እንደሚያገኙ ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

በቅርቡ የዛምቢያና የታንዛኒያ መንግስታት ወደሃገራቸው በህገወጥ መንገድ የሚገቡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቁጥር መጨመር እያሳሰባቸው መምጣቱን መግለጻቸው ይታወሳል።

በሁለቱ ሃገራት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በእስር ቤቶች የሚገኙ ሲሆን፣ የማላዊ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ወደ 120 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሶስት እስር ቤቶች እየተሰቃዩ መሆኑን በመቃወም ዘመቻ መክፈታቸውን መዘገባችን ይታወቃል።

የኢትዮጵያ መንግስት በደረሰ አደጋም ሆነ በእስር ላይ ስለሚገኙ ኢትዮጵያውያን እስካሁን ድረስ የሰጠው ምላሽ የለም።