ኢሳት (ጳጉሜ 4 ፥ 2008)
በዛምቢያ ድንበር በህገወጥ መንገድ ሲጓጓዙ ነበሩ የተባሉ 14 ስደተኞች ኢትዮጵያውያን ላይ የትራፊክ አደጋ ደርሶ ሁለት ኢትዮጵያውያን መሞታቸውን የሃገሪቱ ባለስልጣናት አርብ ገለጡ።
የዛምቢያ ፖሊስ በበኩሉ በተለያዩ ጊዜያው ወደ ዛምቢያ የሚሰደዱና ሃገሪቱ አቋርጠው የሚጓዙ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ እንዳሳሰበው መገልጹን የዛምቢያ መገኛኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በሃገሪቱ የድንበር አካባቢ ደርሶ ነበር ከተባለው የትራፊክ አደጋ የተረፉ 12 ስደተኛ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ወቅት ወደ መዲናይቱ ሉሳካ የተጓጓዙ ሲሆን፣ የሁለቱ ሟች ኢትዮጵያውያን ማንነት መለየቱን ሉሳካ ታይምስ ጋዜጣ ዘግቧል።
በዚሁ የትራፊክ አደጋ ጉዳይ ደርሶባቸው ከነበሩት ኢትዮጵያውያን መካከል ተጨማሪ ሁለት በሆስፒታል የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ሲሆን፣ የአንድ ሟች ስደተኛ ማንነት ተለይቶ አለመታወቁን የዛምቢያ የጸጥታ ሃይሎች ገልጸዋል።
የኢትዮጵያውያን አስከሬን ወደ ኢትዮጵያ ለማጓጓዝ ከአለም አቀፉ የስደተኛ ድርጅት ጋር ምክክር እየተደረገ እንደሚገኝ ሉሳካ ታይምስ ጋዜጣ የፖሊስ ሃላፊዎችን ዋቢ በማድረግ በዘገባው አመልክቷል።
ከአንድ ወር በፊት በዛምቢያ የድንበር አካባቢ በእቃ መጫኛ ተሽከርካሪ ይጓዙ የነበሩ ከ60 በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የመታፈን አደጋ አጋጥሟቸዋል ተብለው መሞታቸው ይታወሳል።
የሃገሪቱ ፖሊስ በበኩሉ በተለያዩ ጊዜያት ወደ ሃገሪቱ የሚገቡና ዛምቢያን ለማቋረጥ የሚጠቀሙ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እየጨመረ በመሄድ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።
በታንዛኒያ፣ ማላዊ፣ ዛምቢያና ሌሎች የደቡባቢው አፍሪካ ሃገራት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወደየሃገሪቱ በህገወጥ መንገድ ገብታችኋል ተብለው ለእስር ተዳርገው እንደሚገኙ የአለም አቀፉ ስደተኛ ድርጅት ይገልጻል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ኢትዮጵያ ወደተለያዩ ሃገራት በመሰደድ ላይ መሆናቸውን ታውቋል።