ኢሳት (መጋቢት 13 ፥ 2008)
በቅርቡ ወደ ዚምባብዌ በህገወጥ መንገድ ገብታችኋል ተብለው በቁጥጥር ስር የዋሉ 13 ኢትዮጵያውያን በእስር ቤት በምግብ እጦት በመሰቃየት ላይ መሆናቸውን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።
የኢትዮጵያውያኑን ጉዳት ለመመልከት ተሰይሞ የነበረ ችሎትም ስደተኞቹ ያቀረቡት የረሃብ ቅሬታ ተከትሎ ጉዳዩን ሳይመለከት ለሌላ ጊዜ መቅጠሩን ክሮኒክል የተሰኘ እለታዊ ጋዜጣ አስነብቧል።
ፍርድ ቤት ቀርበው የነበሩት ስደተኛ ኢትዮጵያውያንም የደረሰባቸውን የምግብ እጥረት ችግር በመግለጽ ከፍርድ ቤቱ ላለመውጣት ቢወስኑም ዳኛው ችግራቸው እንደሚቀረፍ ቃል መግባታቸው ታውቋል።
ይሁንና፣ ኢትዮጵያውያኑ ከችሎት እንደማይወጡ ቢገልጹም የጸጥታ ሃይሎች ተጠርተው ተከሳሾቹ ከችሎቱ እንዲወጡ ማድረጋቸውን ጋዜጣው በዘገባው አመልክቷል።
ኢትዮጵያውያኑ ባቀረቡት የረሃብ ተቃውሞ፣ ችሎቱን የሰረዘው ፍርድ ቤቱም የስደተኞቹን ጉዳይ ዳግም ለመመልከት ለቀጣዩ ሳምንት ቀጠሮን የያዘ ሲሆን፣ ከስደተኞቹ መካከል የ16 አመት ታዳጊ ወጣት እንደሚገኝም ለመረዳት ተችሏል።
በሃገሪቱ የጸጥታ ሃይሎች ከቀናት በፊት በቁጥጥር ስር የዋሉት ኢትዮጵያውያን ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመጓዝ እቅድ እንደነበራቸው ታውቋል።
ዜምባብዌን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በታንዛኒያ፣ ዛምቢያ እና ሌሎች የደቡብ ሃገራት እስር ቤቶች እንደሚገኙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
በቅርቡም የጎረቤት የኬንያ የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት የሃገሪቱ መንግስት ተጨማሪ በጀትን በማጽደቅ ከኢትዮጵያ በሚሰደዱ ሰዎች ላይ ቁጥጥር እንዲደረግ ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል።